የአውሮፓና የአፍሪካ መሪዎች፤ ስደትን ለመግታት በሚያስችል አዲስ ዕቅድ ላይ ተስማሙ

ጉባኤው ላይ ተሳታፊ የሆኑ የአፍሪካ መሪዎች የማነኛውም ስትራቴጂ ማዕከል መሆን ያለበት ድህነትን መታገል ነው ብለዋል [AFP]

ስደትን በሚመለከት ጉባኤ ላይ ተሳታፊ የሆኑ የአራት አውሮፓ ሀገራት መሪዎች፤ ኒጀር እና ቻድ ውስጥ ካሉ ደህንነታቸው የተጠበቁ ቦታዎች ላይ ሆነው ጥበቃ እንዲደረግላቸው የጥገኝነት ጥያቄ የሚያቀርቡ ስደተኞችን ማመልከቻዎች እንደሚቀበሉ ተናግረዋል፡፡

በፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን አስተናጋጅነት በተሰናዳው ጉባኤ ላይ የፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ኢጣሊያ፣ ስፔን፣ ኒጀር፣ ቻድ እና ሊቢያ መሪዎች ተገኝተዋል፡፡ የአውሮፓ መሪዎቹ ከአፍሪካ ወደ ሜዲትራንያን የሚደረገውን የስደተኞች ፍሰት ለመቀነስም ቻድ እና ኒጀር የድንበር ጥበቃቸውን እንዲያጠናክሩ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡

የሰባቱ ሀገራት መሪዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ “ዋና የችግሩን መንስኤዎች መፍታት ይቻል ዘንድ ስደተኞች ከሚመጡባቸው ሀገራት ጋር ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር፣ ስደተኞች ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት ለመከላከል እና ህገወጥ ስደተኞች ወደመጡባቸው ሀገራት የመመለስ አቅም ለማሻሻል እንዲሁም ደግሞ ቀደም ሲል የተደረጉ ስደትን የሚመለከቱ ስምምነቶች ትግበራ በሚመለከት አብረው ለመስራት ስምምነት ላይ” መድረሳቸውን ገልፀዋል፡፡

“ጥገኝነት ለማግኘት መብቱ ያላቸው” ስደተኞች ከኒጀር፣ ቻድ እና ሊቢያ ውስጥ ሆነው ምልመላ እንዲደረግላቸው እንዲሁም ደግሞ በ UNHCR ጥበቃ ስር ሆነው ኒጀር እና ቻድ ውስጥ ወደሚገኙ ሙሉ ለሙሉ ደህንነታቸው የተጠበቁ ተብለው ወደ ተለዩ ቀጠናዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲወሰዱ ፍላጎቱ እንዳላቸው ማክሮን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡

“ሰዎች በጣም አደገኛ በሆነው አካባቢ ላይ ቀጥሎም ደግሞ ሜዲትራንያን ላይ ጉዞ ለማድረግ ብልህ ያልሆነ ድፍረት እንዳይፈፅሙ ማዕከላቱ ይከላከላሉ” ብለዋል ማክሮን፡፡
መሪዎቹ የቀረበው ዕቅድ ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል፤ ምንም እንኳ በተግባር እንዴት እንደሚከወን የሚገልፅ ብዙ ዝርዝር ማብራርያ የሌለው ቢሆንም፡፡ ከጉባኤው በኋላ በወጣው መግለጫ ላይ እንዳሉት፤ አንድ የጋራ ልዑክ ወደ ኒጀር እና ቻድ በቅርቡ ይላካል፡፡
ጉባኤው ላይ ተሳታፊ የሆኑ የአፍሪካ መሪዎች፤ የማነኛውም ስትራቴጂ ማዕከል መሆን ያለበት ድህነትን መታገል ነው ብለዋል፡፡

“ሁላችንም የሚደርሰውን ጉዳት፣ በረሃ ላይ የሚሞቱትን አፍሪካውያን ቁጥር፣ ሜዲትራንያንን የሚያቋርጡ አፍሪካውያን ቁጥር ለመቀነስ ቁርጠኞች ነን” ብለዋል የቻዱ ፕሬዝደንት ኢድሪስ ዴቢ፡፡

“ምንግዜም ቢሆን ዋናው ችግር ሆኖ የሚዘልቀው ልማት ነው፡፡ አቅም ያስፈልገናል” ሲሉ አክለዋል፡፡
ሰኞ ’ለት ከኢጣሊያው የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በሮማ የተገናኙት የሊቢያ፣ ቻድ፣ ኒጀር እና ማሊ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች የፓሪሱ ጉባኤ አጀንዳ “በአውሮፓና በአፍሪካ መካከል አዲስ የግንኙነት ጅማሬ ሊፈጥር የሚችል” ነው ብለዋል፡፡