አንድ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪ በኢጣሊያ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት
የፎቶ ምንጭ: ሬውቶርስ፡፡ መኪኖች በሱዳን እና ሊቢያ መካከል በሚገኘው የሰሃራ በረሃ ስደተኞችን ሲያጓጉዙ፡፡
አንድ ሶማሊያዊ ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ በርካታ ስደተኞች ላይ በፈፀመው የአስገድዶ መድፈር፣ ማሰቃየትና ግድያ ወንጀል በኢጣሊያ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት፡፡ ጥቃቱን ያደረሰው ከትሪፖሊ በስተደቡብ-ምስራቅ 100 ማይሎች ርቀት ላይ በሊቢያ በረሃ ባኒ ዋሊድ በተባለ አካባቢ በሚገኘው የእስር ማእከል ውስጥ ነው፡፡
የ 22 ዓመት ዕድሜ ያለውና ከመቋዲሾ የመጣው ይህ ዑስማን ማታሙድ የሚባለው ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪ ሜዲትራንያንን ተሻግሮ ኢጣሊያ ከገባ በኋላ ጥገኝነት ጠያቂ በመምሰል እራሱን ለመሸሸግ ሞክሮ ነበር፡፡ እንደርሱ ሶማልያውያን የሆኑ የሀገሩ ሰዎች ለይተው ካወቁት በኋላ ነበር ሚላን ከተማ ውስጥ ከአንድ ዓመት በፊት በቁጥጥር ስር የዋለው፡፡ የዜና ምንጮች እንደሚሉት፤ በወቅቱ ስደተኞች ተሰብስበው ሊደበድቡት ሲሉ ነበር የኢጣሊያ ፖሊስ ደርሶ ያስጣለው፡፡
ቴሌግራፍ ጋዜጣ እንደዘገበው፤ አንዲት ልጃገረድ ማታሙድ በተደጋጋሚ አስገድዶ እንደደፈራት ለፍርድቤት ተናግራለች፡፡ “የመጀመርያው ሌሊት ላይ፤ ወደ መጠለያው መጥቶ ያዘኝ፤ ሁሉም ሰው እያየ ለብሶቼን ከላየ ላይ ቀዳድዶ ጣለብኝ” ብላለች፡፡
ሌሎች ስደተኞችም ተከሳሹ ሊቢያ በሚገኘው የእስር ማዕከል ውስጥ እንዴት እንደደፈራቸው እና እንዳሰቃያቸው በማብራራት መስክረውበታል፡፡ ማታሙድ ይህን የጭካኔ ተግባር ለምን እንደሚያከናውን የተጠቀሰው አንዱ ምክንያት የስደተኞቹ ቤተሰቦች በሜዲትራንያን በኩል ለሚደረገው ጉዞ ተጨማሪ ገንዘብ እንዲከፍሉ ለማስገደድ ነው፡፡
ስደተኞች በድንጋይ መመታታቸውን፣ በኤሌክትሪክ መሰቃየታቸውን እና ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪው በተበዳዮቹ ቆዳ ላይ ላስቲክ በማቅለጥ እንዴት እንዳሰቃያቸው ሲመሰክሩ በሚላኑ ፍርድ ቤት የተሰየሙት ዳኞች አድምጠዋል፡፡
የሚላኑ ፍርድ ቤት ማታሙድ ልጃገረዶችን ጨምሮ ስደተኞችን በመግደል፣ በመጥለፍና ፆታዊ ጥቃት በማድረስ ወንጀሎች ጥፋተኛ ሆኖ አግኝቶታል፡፡ ሶስት የመጀመርያ የእስር ዓመታቱን ለብቻው ተነጥሎ እንዲታሰርም በተጨማሪ ቅጣት ተላልፎበታል፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ