90 ስደተኞች በሊቢያ የባህር ጠረፍ ሰጥመው እንዳይሆን ተሰግቷል
የፎቶ ምንጭ: AP – ከመጠን በላይ የታጨቀች የስደተኞች ጀልባ በሜዲትራንያን ባህር ላይ
የተባበሩት መንግስታት የስደት ጉዳዮች ኤጀንሲ የሆነው IOM፤ በሰጠው መግለጫ ላይ እንዳስታወቀው፤ በፈረንጆቹ የካቲት 2 ማለዳ ላይ አንዲት የስደተኞች ጀልባ በሊቢያ የባህር ጠረፍ አቅራቢያ ስትሰምጥ በግምት 90-100 የሚሆኑ ስደተኞች ተሳፍረውባት እንደነበረ ተጠቁሟል፡፡
የ IOM የሊቢያ ፅህፈት ቤት ባልደረባ የሆኑት ኦሊቪያ ሄደን እንደሚሉት፤ 10 የስደተኞች ሬሳ ከትሪፖሊ በስተምዕራብ 100 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው የዛውራ ከተማ አቅራቢያ በሚገኙ የሊቢያ የባህር ዳርቻዎች ላይ ተገፍቶ ወጥቷል፡፡
የዛውራ ከተማ የደህንነት መስሪያ ቤት የአካባቢው ሰዎች ባህር ዳርቻው ላይ ሬሳ ማየታቸውን ጥቆማ እንዳደረሱት ተናግሯል፡፡ ፖሊሶች አካባቢው ላይ ሲደርሱ፤ የ 10 ፓኪስታናውያን እና የአንዲት ሊብያዊት ሴት ሬሳ አግኝተዋል፡፡
ሁለት ሰዎች ወደ ዳርቻው ዋኝተው በመውጣት ከአደጋው በሂወት መትረፍ የቻሉ ሲሆን፤ አንድ ሌላ ሰው ደግሞ አሳ አጥማጆች ታድገውታል፡፡ በሂወት መትረፍ የቻሉት አንድ ሊብያዊና ሁለት ፓኪስታናውያን እንዳሉት አብዛኞቹ የሰጠሙት ሰዎች የፓኪስታን ዜጎች ናቸው፡፡
የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳረጋገጠው 16 ፓኪስታናውያን በዚሁ የጀልባ መስጠም አደጋ በሊቢያ የባህር ጠረፍ አቅራቢያ የሞቱ ሲሆን ከነዚህ የ 12 ሬሳ ተግኝቷል፡፡
የሚኒስትር መስሪያቤቱ ቃልአቀባይ የሆኑት መሃመድ ፈይሰል ለአሶሼትድ ፕረስ እንደተናገሩት የፓኪስታን ዲፕሎማቶች ተጨማሪ መረጃዎችን ለመሰብሰብ ወደዚሁ የሊቢያ የባህር ጠረፍ አካባቢ አቅንተዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ በዚሁ አደጋ የሞቱት ፓኪስታናውያን ሬሳ ወደሀገራቸው ለመመለስ መንግስታቸው ጥረት ያደርጋል፡፡
ፈይሰል ቆየት ብለው የሰለባዎቹን ስም እና ሌላ ዝርዝር ትዊተር ላይ አሰራጭተዋል፡፡ ስምንት ሬሳዎች የተገኙና ማንነታቸው የተለየ ሲሆን አራቱ ግን በጓደኞቻቸው ተለይተው የታወቁ ቢሆንም የመታወቂያ ሰነዳቸው እስካሁን አልተገኘም፡፡ እሳቸው በተጨማሪ እንደገለፁት፤ የስድስት ሰዎች መታወቂያ ሰነዶች የተገኘ ቢሆንም፤ ሬሳቸው ግን አሁንም አልተገኘም፡፡
እነዚህ የተረጋገጡት የሟች ቁጥሮች በፈረንጆቹ 2018 የመጀመርያው ወር ላይ በሜዲትራንያን ባህር የሞቱ ሰዎችን ቁጥር 246 አድርሶታል፡፡
እስካሁን ድረስ ሰላሳ የአፍሪካ ቀንድ እና ሰባት የሰሜን አፍሪካ ስደተኞች በዚሁ ዓመት መጥፋታቸው መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡
የማካከለኛው ሜዲትራንያን መስመር እየተባለ በሚጠራውና ሊቢያን ከጣሊያን ጋር በሚያገናኘው መተላለፊያ በኩል ወደ አውሮፓ ለመድረስ ሙከራ የሚያደርጉ ስደተኞች የሚገጥሟቸው እጅግ ፈታኝ አደጋዎችን በተመለከተ IOM ተደጋጋሚ ማስጠንቀቅያዎችን አውጥቷል፡፡
“የአየር ሁኔታው የተረጋጋ እንደነበር አውቀናል፤ ስለዚህም ግድየለሽ መባል የሚያንሳቸው ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ጀልባዋን ከመጠን በላይ ነው አጭቀው የጫኗት” ሲሉ የ IOM ባልደረባ የሆኑት ሊዮናርድ ዶይል ለአልጀዚራ ተናግረዋል፡፡ “ሰዎች እንዲሰሙት ማድረግ አለብን፤ በየትኛውም የዓለም አቅጣጫ የሚገኙ አማራጭ የሌላቸው የሚመስላቸው ሰዎች፤ ወደተሻለ ሂወት እየመጡ የሚመስላቸውና በማህበራዊ ሚዲያ መሰል ፅሑፍ ያነበቡ ሰዎች፤ እውነታው የተለየ እንደሆነ ልንነግራቸው ይገባል” ይላሉ፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ