ሴቭ ዘ ችልድረን ስደተኞችን ከባህር ላይ የመታደግ እንቅስቃሴውን ገታ

የፎቶ ምንጭ: ሴቭ ዘ ችልድረን፡፡ ቮስ ሄስቲያ የምትባለው መርከብ፡፡

ዓለምአቀፍ ሰብአዊ እርዳታ ሰጪ ቡድን የሆነው ሴቭ ዘ ችልድረን በፈረንጆቹ ጥቅምት 23 ላይ እንዳስታወቀው በሜዲትራንያን ባህር ሲያከናውን የነበረውን ስደተኞችን የመታደግ እንቅስቃሴውን ገትቷል፡፡

“ውሳኔው የተደረገው አውሮፓ ለመድረስ በመካከለኛው ሜዲትራንያን በኩል ለማቋረጥ የሚሞክሩ ስደተኞች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን በከፍተኛ ጥንቃቄ ካጤነ በኃላ፤ እንዲሁም ደግሞ በአካባቢው የሚደረጉ ስደተኞችን ከባህር ላይ የመታደግ እንቅስቃሴዎች ውጤታማነትና ደህንነት ላይ ለውጥ መኖሩን በመገንዘብ ነው” ብለዋል የሴቭ ዘ ችልድረን ዋና ዳይሬክተር ቫሌርዮ ኔሪ፡፡

የሴቭ ዘ ችልድረን መርከብ ስራ ከጀመረችበት ካለፈው ዓመት የመሰከረም ወር ጀምሮ ከ 10,000 በላይ ስደተኞችን ከባህር ላይ ታድጋለች፡፡
የኢጣሊያ መንግስት በሜዲትራንያን ስደተኞችን የመታደግ ስራ የሚያከናውኑ ቡድኖች ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ስደተኞቹን ባህር ላይ ይታደጓቸዋል በማለት ደካማ በሆኑ እና ከአቅም በላይ በታጨቁ ጀልባዎች ላይ አሳፍረው እንዲልኳቸው ያበረታታሉ ሲል ከሷል፡፡

ሴቭ ዘ ችልድረን ስደተኞችን ከባህር ላይ የመታደግ እንቅስቃሴ መግታቱን ባሳወቀበት ቀን፤ የኢጣሊያ ፖሊስ የእርዳታ ድርጅቱ ተከራይቶ ሲጠቀምባት የነበረችውን ቮስ ሄስቲያ የተባለችው መርከብ ላይ ብርበራ አድርጓል፡፡ ብርበራው እንዲደረግ ያዘዘው በሜዲትራንያን ላይ ሲከናወኑ የነበሩ የነፍስ አድን ስራዎች ላይ ምርመራ ሲያደርግ የነበረው የሲሲልያዊቷ የወደብ ከተማ የሆነችው የትራፓኒ ከተማ ዓቃብያነ ህግ ናቸው፡፡

ነገር ግን፤ የእርዳታ ድርጅቱ እንቅስቃሴውን ለመግታት የወሰነው ፖሊስ በሲሲልያዊቷ የካታኒያ ወደብ መርከባቸው ላይ ፍተሻ ከማድረጉ ቀደም ብሎ መሆኑን እና እየተደረገበት ያለ ምርመራ እንደሌለም ተናግሯል፡፡

ሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ የእርዳታ ድርጅቶችም የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ እየወሰደ ያለው ጠንካራ እርምጃ እና ወደ አውሮፓ የሚደርሱ ስደተኞች ቁጥር ማሽቆልቆሉን በመጥቀስ የሚያከናውኑትን የነፍስ አድን እንቅስቃሴ አቁመዋል፡፡