ጀልባ ላይ የታጨቁ ስደተኞች በሊቢያ ጠረፍ ሂወታቸው አለፈ
የስፔኑ ምግባረ ሰናይ ድርጅት ‘ፕሮአክቲቫ ኦፕን አርምስ’ ሰራተኞች በሜዲትራንያን የሊቢያ ባህር ጠረፍ ላይ ሂወቷ የታደጉላት ሴት ስታለቅስ፡፡ ፎቶ: በሳንቲ ፓላኪዮስ/AP
የነፍስ አድን ሰራተኞች፤ በሊቢያ የባህር ጠረፍ ስትናውዝ በነበረች የፕላስቲክ ጀልባ ላይ፤ ሁለት እርጉዝ ሴቶች የሚገኙባቸው የ 13 ስደተኞች ሬሳ ማግኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡
“በአጠቃላይ አስራ ሶስት ሬሳ:: እነዚህ ሰዎች ስም፣ የአባት ስም፣ እናት፣ አባት፣ ጓደኛ እና ሂወት ነበራቸው እኮ” ብሏል የስፔኑ ምግባረ ሰናይ ድርጅት ‘ፕሮአክቲቫ ኦፕን አርምስ’ ባወጣው መግለጫ፡፡
ስደተኞቹ ሂወታቸው ያለፈው ቢያንስ 181 ሰዎችን በመጫን ከሊቢያ ወደ አውሮፓ ለመሻገር ጉዞ የጀመረችው የፕላስቲክ ታንኳ ከተንቀሳቀሰች ከ 24 ሰዓታት በኋላ ነው፡፡ ከሟቾቹ መካከል ስምንቱ ሴቶች ናቸው፤ ከነዚህም ደግሞ ሁለቱ እርጉዞች ነበሩ፡፡
የፕሮአክቲቫ የህክምና ቡድን፤ ስደተኞቹ ሂወታቸው ያለፈው ባጋጠማቸው የባህር ላይ ህመም ወደ ወለሉ እየተዝለፈለፉ ከወደቁ በኋላ ነው የሚል መላምት አስቀምጧል፡፡ የጀልባይቱ ነዳጅ ከጨዋማው ውሃ ጋር ሲቀላቀል የሚፈጥረውን መርዛማ አየር በትንፋሻቸው ስበው በማስገባታቸው ምክንያት ታፍነው ሊሆን ይችላል፡፡
“ከጀልባው ውጪ ሰምጠው አይደለም የሞቱት፤ ጀልባዋ ውስጥ ታፍነው እንጂ” ብለዋል የፕሮአክቲቫ ኦፕን አርምስ የዘመቻ መሪ ሪካርዶ ጋቲ፡፡
የስድስት ህፃናት ሂወት መታደግ የተቻለ ሲሆን፤ ከመካከላቸው በዕድሜ ትልቅ የሆነው የአምስት ዓመት ህፃን ይገኝባቸዋል፡፡
በሂወት ከተረፉት ሴቶች ሁለቱ፤ ከሊቢያ ከመሄዳቸው በፊት በተደጋጋሚ ፆታዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው እንዲሁም ደግሞ “በጣም እንደተደበደቡ” ለህክምናው ቡድን ተናግረዋል፡፡ ፕሮአክቲቫ እንዳስታወቀው፤ በአንዳንድ ሴቶች ላይ የታየው መጋጋጥ ምናልባት ተደፍረው ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁም ነው፡፡
የተባበሩት መንግስታት መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በዚህ ዓመት ብቻ እስካሁን ድረስ ወደ አውሮፓ ለመግባት የሞከሩ 2,400 ሰዎች ሜዲትራኒያን ባህር ላይ ሂወታቸውን አጥተዋል፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ