በሶስት ወራት ውስጥ ከ 13,000 በላይ ናይጄርያውያን ከሊቢያ እንዲወጡ ተደረገ

የናይጄርያ መንግስት ከህዳር እስከ ጥር 2010 ዓ.ም ባሉት ወራት ውስጥ ከ 13,000 በላይ ዜጎቹን ከሊቢያ ማስወጣቱን ጥር 16 ላይ አስታውቋል፡፡
ሊቢያ ውስጥ ከሚገኙ አጠቃላይ አፍሪካውያን ስደተኞች ናይጄርያውያን በብዛት ቀዳሚውን ስፍራ ይዛሉ፡፡ በጥር ወር መጀመርያ፤ ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ከሊቢያ መመለስ የሚፈልጉ ዜጎቿን በራሷ ተነሳሽነት ነው ማስወጣት የጀመረችው፡፡

“ዋናው ዓላማ እነዚህን ናይጄርያውንያ ዜጎች በተቻለ ፍጥነት ወደሀገራቸው መመለስ ነው፤ እኛም እዚህ ዓላማ ላይ አተኩረን ነው የምንሰራው” ነበር ያሉት የናይጄርያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆፍሪ ኦኜየማ በጥር ወር መጀመርያ ላይ ትሪፖሊን በሚጎበኙበት ወቅት ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፡፡
“ፕሬዝደንታችን እዚህ የሚገኙ ሁሉንም ናይጄርያውያንን ወደሀገራቸው ለመመለስ አስፈላጊ የሆነውን ድጋፍ ሁሉ አቅርበዋል” ብለዋል፡፡
በጥቅምት ወር ሲኤንኤን በሊቢያ የባርያ ንግድ ጨረታ ሲከናወን የሚያሳይ ምስል ካሰራጨ በኋላ ወደሀገራቸው ከተመለሱት 13,000 ስደተኞች በተጨማሪ፤ ናይጄርያ 5,500 ተጨማሪ ስደተኞችን ለመመለስ እቅድ አላት፡፡ ነገር ግን፤ መሬት ላይ ያለው ሁኔታ፤ እቅጩን ቁጥር ለማረጋገጥ ከባድ ያደርገዋል፡፡
“ትክክለኛ ቁጥር ለማግኘት አስቸጋሪ ከሚያደርጉት ፈተናዎች አንዱ፤ አንዳንዶቹ በማዕከላዊ መንግስቱ ስር በሚገኙ ካምፖች ውስጥ ነው ያሉት፤ አንዳንዶች ደግሞ ከነዚህ ካምፖች ውጭ መሆናቸው ግልፅ ነው፤ አንዳንዶች ደግሞ ለመድረስ አስቸጋሪ በሆኑና ማዕከላዊ መንግስቱ ሙሉ ቁጥጥር እና ስልጣን በሌለበት አካባቢዎች የሚገኙ ናቸው” ብለዋል ኦኜየማ፡፡

ባለፈው ዓመት የሓምሌ ወር ላይ፤ የታጠቁ አካባቢያዊ ቡድኖች እና የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ሃይል ስደተኞች ከሀገሪቱ እንዳይወጡ መከልከል ከጀመሩበት ግዜ አንስቶ ብዙ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች በሊቢያ መሄጃ አጥተው የቆዩ ሲሆን፤ በዚህም ግዜ ጥቃት እና አስገዳጅ ስራን የመሳሰሉ አስከፊ ሁኔታዎች ይደርሱባቸዋል፡፡
ጥቅምት ወር ላይ፤ መጠነ ሰፊ የስደተኞች ጥቃት፣ የቆሸሹና ከመጠን በላይ የተጨናነቁ በሊቢያ የሚገኙ የእስር ማዕከላት፣ እንዲሁም ደግሞ የባርያ ንግድ ጨረታን የሚመለከቱ ዘገባዎች መውጣታቸው በሊቢያ መሄጃ አጥተው የሚገኙ ስደተኞችን የሚመለከተው አሳሳቢነት እንደገና በዓለምአቀፍ ደረጃ እንዲነሳ አድርጓል፡፡
ዓለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት፤ ሊቢያ ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች ቁጥር 432,574 ነው ብሎ ቢጠቅስም፤ ከ 700,000 እስከ አንድ ሚልዮን ሊሆኑ እንደሚችል ግምቱን ያስቀምጣል፡፡

በ 2017፤ ዓለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት (IOM) 19,370 ስደተኞችን ከሊቢያ ወደየ ሀገሮቻቸው መልሷል፡፡ ብዙ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች የተመለሱባቸው አራት ሀገራት ናይጄርያ፣ ጋምቢያ፣ ጊኒ-ኮናክሪ እና ማሊ ናቸው፡፡