ከ 19,000 በላይ ስደተኞች በ 2017 ከሊቢያ ወደየ ሀገራቸው ተመለሱ
ከሊቢያ ወደ ኒጀር የተመለሱ ስደተኞች፡፡ የፎቶ ምንጭ: ዓለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት
በፈረንጆቹ 2017 ከ 19,000 በላይ የሚልቁ ስደተኞች በዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አማካኝነት ከሊቢያ ወደየ ሀገሮቻቸው እንዲመለሱ ተደርገዋል፡፡
በህዳር ወር አጋማሽ ሲኤንኤን አፍሪካውያን ስደተኞች በሊቢያ ባሮች ሆነው ሲሸጡ የሚያሳየውን የቪድዮ ምስል ካሰራጨ በኋላ እንዲሁም ደግሞ ለሌላ ኢሰብአዊ አያያዞች መጋለጣቸውን የሚያሳዩ ሪፖርቶች መውጣታቸውን ተከትሎ፤ ሀገራት ዜጎቻቸውን ከሊቢያ የእስር ማዕከላት አስወጥተው ወደየ ሀገሮቻቸው ለመመለስ የሚያደርጉትን ጥረት እያፋጠኑ ነው፡፡ ብዙዎች ‘ገሃነም’ እያሉ በሚጠሯቸው የእስር ማዕከላት ውስጥ ስደተኞች በጣም አስከፊ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነው የህግ ከለላ ሳያገኙ እየተሰቃዩ ለረጅም ግዚያት ይታሰራሉ፡፡
በሊቢያ የሚገኘው የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (IOM)፤ የስደተኞች በበጎፈቃደኝነት የመመለስ መርሃግብር አስተባባሪ የሆኑት ጁማ ቤን-ሁሴን በቅርቡ ለሺንዋ የዜና አገልግሎት እንደተናገሩት፤ ድርጅታቸው 19,370 ለሚሆኑ ስደተኞች በአየር ወደ 27 የአፍሪካና የኤስያ ሀገራት ዋና ከተሞች በማጓጓዝ ስደተኞቹ ወደየ ሀገሮቻቸው እንዲመለሱ ድጋፍ አድርጓል፡፡
በህዳር ወር መጨረሻ ላይ የአፍሪካ እና የአውሮፓ መሪዎች ስደተኞችን ከሊቢያ በአስቸኳይ ለማስወጣት መስማማታቸውን ተከትሎ፤ በሊቢያ የእስር ማዕከላት ውስጥ መሄጃ አጥተው የሚገኙ ስደተኞችን ወደየ ሀገሮቻቸው ለመመለስ የሚደረገው ጥረት በፈረንጆቹ አዲስ ዓመትም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
የናይጄርያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ጆፍሪ ኦንያማ፤ በዚሁ ስምምነት መሰረት ሀገራቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ወደቤታቸው ማጓጓዝ መጀመርዋን እና ሁሉም ወደሀገራቸው መመለስ የሚፈልጉ ዜጎቻቸው ከቤታቸው እስኪገቡ ድረስ በአየር የማጓጓዝ ስራው እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ