አንድ ኤርትራዊ ስደተኛ በምግብ እጦት ምክንያት ህይወቱ አለፈ
የነፍስ አድን ሰራተኞች ከሜዲትራንያን ባህር የታደጉት አንድ ኤርትራዊ ስደተኛ ጣልያን ከደረሰ ከሰዓታት በኋላ በነበረበት ከፍተኛ የምግብ እጥረት ህይወቱ ሊያልፍ መቻሉን የስፔን የዕርዳታ ድርጅት መጋቢት 4 ላይ አስታውቋል፡፡
ይህ ሰገን የሚባል የ 22 ዓመት ወጣት በመጋቢት 2 ፕሮአክቲቫ ኦፕን አርምስ በተባለው የስፔን ዕርዳታ ድርጅት በምትንቀሳቀሰው መርከብ የነፍስ አድን ሰራተኞች ከታደጓቸው 93 ስደተኞች መካከል አንዱ ነበር፡፡
ሰገን በአንድ የሲሲልያ ሆስፒታል ማረፉን በትዊተራቸው ላይ የገለፁት የፕሮአክቲቫ ኦፕን አርምስ መስራች የሆኑት ኦስካር ካምፕስ ናቸው፡ “ኤርትራዊ ነው ለ 19 ወራት በሊቢያ ታስሮ ቆይቷል” በማለት፡፡
“ለምን ያህል ግዜ ምግብ ሳይቀምስ እንደቆየ ማን ያውቃል፡፡ ሰውነቱ እጅጉን ተጎሳቁሎና ከስቶ አጥንት ነበር የቀረው” ብለዋል ዶክተር ካርሜሎ ስካርሶ ለ ላ ሪፓብሊካ ጋዜጣ ሲናገሩ፡፡
“እጅጉን የተዳከሙ ስደተኞችን አይተን እናውቃለን፤ ይሄኛው ግን ከመጠን በላይ ነው” ብለዋል፡፡
ወጣቱ በምግብ እጦት እና ከፍተኛ በሆነ የአተነፋፈስ ችግር እየተሰቃየ እጅግ በጣም በአደገኛ በሆነ አካላዊ ሁኔታ ውስጥ ነበር፡፡ ልክ መርከቧ ወደብ ላይ እንደቆመች፤ ከሰዓታት በኋላ ወደሞተበት ሆስፒታል ነው የተወሰደው፡፡
ሰገን የነፍስ አድን ሰራተኞች በታደጉት በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ለህልፈት ቢዳረግም፤ ኦፕን አርምስ እንዳለው ከሱ በባሰ መልኩ በምግብ እጦት የተጎዱና ከመርከቧ በአስቸኳይ መውጣት የነበረባቸው ሌሎች ሁለት ሰዎች ነበሩ፡፡
የዕርዳታ ድርጅቷ መርከብ ሰራተኞች የታደጓቸው ስደተኞች አብዛኞቹ በምግብ እጦት፣ ድካም እና ውሃ ጥም ሲሰቃዩ የቆዩ ናቸው፡፡
“ትናንት አስከፊ ነገር ነው ያየነው፤ በጣም አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ በምግብ እጦት መጎዳትን ያየነው እንዳለመታደል ሆኖ ሂወቱን ባጣው ወጣት ላይ ብቻ ሳይሆን አብረውት ሲጓዙ በነበሩት ስደተኞችም ጭምር ነው” በማለት የፖዛሎ ከተማ ከንቲባ የሆኑት ሮቤርቶ አማቱና ለ ላ ሪፓብሊካ ጋዜጣ ተናግረዋል፡፡
“ሁሉም አጥንትና ቆዳ ብቻ ነው የቀራቸው፤ ከድሮ የናዚ ማጎርያ ጣቢያ የወጡ ነው የሚመስሉት … በጣም አስደንጋጭ ነበር” ብለዋል አማቱና፡፡
“አብዛኞቹ ስደተኞች እከክ ነበረባቸው፤ ነገር ግን እጅጉን ያስደነገጠን ነገር አካላዊ ሁኔታቸው ነበር፡፡ ምንም ስጋ ያልቀራቸው ወንዶች፣ ሴቶች እና ህፃናት፤ የአጥንት ክምር ብቻ” ሲሉ ይጨምራሉ፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ