የአውሮፓና የአፍሪካ ሚኒስትሮች በአስከፊው የስደተኞች ሁኔታ ላይ መከሩ

የፎቶ ምንጭ: ሬውቶርስ/አህመድ ጃላህ፡፡ በፈረንጆቹ ህዳር 6 -2017 ላይ የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች ትሪፖሊ ላይ የታደጓቸው ስደተኞች የባህር ሃይሉ ጣቢያ ላይ ሲደርሱ፡፡

በፈረንጆቹ ህዳር 13፤ ከ 13 የአፍሪካና የአውሮፓ ሀገራት የመጡ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንዲሁም ደግሞ የዓለምአቀፍ ተቋማት ተወካዮች ሲዊዘርላንድ ላይ ተሰብስበው ነበረ፤ ይህም ደግሞ ከሰሜን አፍሪካ እስከ አውሮፓ ባለው የስደት መስመር ላይ የሚያጋጥሙትን እጅግ አሳሳቢ ፈተናዎችን በተመለከተ አስቸኳይ እልባት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ለመምከር ነው፡፡

ስብሰባው ላይ የተወከሉት 13 ሀገራት አልጄርያ፣ ኦስትርያ፣ ቻድ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣልያን፣ ሊብያ፣ ማሊ፣ ማልታ፣ ኒጀር፣ ስሎቬንያ፣ ስዊዘርላንድ እና ቱኒዝያ ናቸው፡፡ እነዚህ ሀገራት የመካከለኛው ሜዲትራንያን ተጠሪ ቡድን በመባል የሚታወቀው ስብስብ አባላት ሲሆኑ በመካከለኛው ሜዲትራንያን በሚደረገው ስደት ተፅዕኖ የሚደርስባቸው የአውሮፓና የአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን የመረጃ ልውውጥ የሚያቀላጥፍ ነው፡፡ የአውሮፓ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ኤጀንሲ (UNHCR)፣ ዓለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት (IOM) እና ዓለምአቀፉ የቀይ መስቀል ማህበር ኮሚቴ (ICRC) ተወካዮችም ስብሰባው ላይ ተሳትፈዋል፡፡

የስብሰባው ዓላማ በሊቢያ የሚገኙ የስደተኞች የእስር ማእከላትን በተለይ ለሴቶች፣ ህፃናት እና ጠባቂ ለሌላቸው ታዳጊዎች በሚመች መልኩ ማሻሻል እና ከእስር ውጭ አማራጮች ማፈላለግን ያካትታል፡፡ ስደተኞች በበጎፈቃደኝነት ወደሀገራቸው እንዲመለሱ ማበረታታት፣ የስደትን መንስኤዎች ለይቶ ማወቅ፣ የኢኮኖሚ አማራጮችን መፍጠር እንዲሁም የትምህርት እና የልምምድ ዕድሎችን የመሳሰሉ አማራጭ የስደት መንገዶችን በተመለከተም ምክክር ተደርጓል፡፡

ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ ስደተኞች ከለላ ለመስጠት የሚያስችል የጋራ አዋጅ በተሳታፊዎቹ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ በመካከለኛው ሜዲትራንያን የስደት መስመር ላይ የጥገኝነት እና የከለላ መዋቅሮች እንዲጠናከሩና ህገወጥ የሰው ዝውውርን ለመዋጋት የሚወሰዱ እርምጃዎች እንዲሻሻሉ አዋጁ ጥሪ ያቀርባል፡፡

በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በዚሁ ቀጠና ላይ እጅግ አስከፊ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኙ ሲሆን በህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች እጅ ወድቀው ለዝርፍያ፣ ጥቃት እና ስጋት ይጋለጣሉ፡፡ ብዙዎች ይህን ጉዞ በማድረግ ላይ እንዳሉ በበረሃ ላይ እና የሜዲትራንያን ባህርን ሲያቋርጡ ሂወታቸውን ያጣሉ፡፡
“በጣም ጥልቅ ውይይት ነው ነው ያደረግነው፤ ምክንያቱም የተነሱት ጥያቄዎች እጅግ ጠንካራ ስለሆኑ፡፡” ብለዋል ይህን ስብሰባ ያስተናገደችው የስዊዘርላንድ የፍትህ ሚኒስቴር የሆኑት ሲሞኔታ ሶማሩጓ ከስብሰባው በኋላ፡፡ “ለዚህም ነው ስደተኞችን ከለላ መስጠት ላይ ትኩረት ያደረግነው፡፡ የተለያየ አመለካከት ያላቸው ብዙ ሰዎች ውይይቱ ላይ ተሳታፊ ናቸው፤ ነገር ግን በአንድ ነጥብ ላይ ሁላችንም ተስማምተናል … የስደተኞችን ሁኔታ ማሻሻል፤ በተለይም ሊብያ ውስጥ ላሉት፡፡”