በስደተኞች መካከል በተነሳ ረብሻ ኤርትራውያን ጉዳት ደረሰባቸው
የፎቶ ምንጭ: AP / በኤርትራውያንና አፍጋናውያን ስደተኞች መካከል በፈረንሳይ ካሌይ አካባቢ በተነሳ ግጭት አራት ኤርትራውያን የከፋ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
በሰሜናዊ ፈረንሳይ ካሌይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኙ ኤርትራውያን እና አፍጋናውያን ስደተኞች መካከል በተነሱ ሶስት የተለያዩ ግጭቶች ከ 16 እስከ 18 ዓመት ዕድሜ ያላቸው አምስት ኤርትራውያን በጥይት ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን አራቱ ደግሞ የከፋ ጉዳት አጋጥሟቸዋል፡፡ ጉዳቱ የደረሰባቸው አራት ሰዎች አንገታቸው፣ ደረታቸው፣ ሆዳቸው እና የጀርባ አጥንታቸው ላይ በተኩስ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ሌሎች 22 ሰዎችም በዚሁ የተነሳ ህክምና ገብተዋል፡፡
ከተኩሱ በኋላ፤ ሁለት ሌሎች ግጭቶች ተከተሉ፡፡ ሁለተኛው ግጭት ያጋጠመው 150 እስከ 200 የሚሆኑና ብረት እና ዱላ የታጠቁ ኤርትራውያን 20 ከሚሆኑ አፍጋናውያን ጋር በመጋጨታቸው ተጨማሪ ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት ሆኗል፡፡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት፤ ለሁለተኛው ግጭት መንስኤ የሆነውና ምግብ ለመበቀበል ተሰልፈው በነበሩ ኤርትራውያን ስደተኞች ላይ ተኩስ የከፈተው የ 37 ዓመት ዕድሜ ያለው አፍጋናዊ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪ እንደሆነ ተጠርጥሯል፡፡
የካሌይ ከንቲባ የሆኑት ናታሻ ቦቻርት እንዳሉት ከተማቸው በህገወጥ ቡድኖች ግጭት ፈተና ገጥሟታል፡፡
“በግልፅ እንደሚታየው በወሮበሎች ቡድን የተደራጀውን ይህን በአንዳንድ ስደተኞች መካከል እየጨመረ የመጣውን ግጭት እያዩ የሚያደርጉት የጠፋባቸው ሰዎች እዚህ ውስጥ ይኖራሉ” ብለዋል የፈረንሳይ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ዤራርድ ኮሎምብ ሬውቶርስ እንደዘገበው፡፡
ታዋቂ የሆነው የካሌይ “ጫካ” በፈረንጆቹ 2016 ላይ እንዲፈርስ ቢደረግም፤ አሁንም ቢሆን እስከ 800 የሚደርሱ ስደተኞች አካባቢው ላይ እየኖሩ ነው፤ ወደ እንግሊዝ እንገባ ይሆናል የሚል ተስፋ በማድረግ፡፡
ስደተኞች ይህን ጉዞ ለማድረግ እስከ 3,000 ዩሮ ድረስ እንዲከፍሉ በህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ይጠየቃሉ፡፡ የፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ካሌይ ውስጥ ለሚነሱት ግጭቶች እነዚህን ህገወጥ የሰው አዘዋሪዎች ይወቅሳሉ፡፡
ሚኒስትር ኮሎምብ በተጨማሪ እንዳሉት፤ የአካባቢው የዕርዳታ ድርጅቶች ለስደተኞች የሚያደርጉትን የምግብ ስርጭት መንግስት ራሱ ለመቆጣጠርና ምግብ የማከፋፈል ስራው ከከተማዋ ውጭ እንዲከናወን ለማድረግ ዕቅድ አለው፡፡ በሚኒስትሩ ገለፃ መሰረት፤ ይህ መሆኑ ስደተኞች ካሌይ ውስጥ እንዳይሰበሰቡ ያግዛል፡፡
ባለፈው ወር፤ የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማንዌል ማክሮን “በምንም ሁኔታ እዚህ ቦታ ላይ ዳግም ሌላ ‘ጫካ’ እንዲፈጠር አንፈቅድም” ሲሉ ይፋ አድርገዋል፡፡ ይህን ያሉት ከእንግሊዝ ጋር የተደረገውን አዲስ የድንበር ጥበቃ ስምምነትን ይፋ ለማድረግ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ነበር፡፡ ይህ ስምምነት በካሌይ የተጠናከረ ጥበቃ እንዲኖር የሚያደርግ ነው፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ