የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ በአንድ ቀን ከአንድ ሺህ በላይ ስደተኞችን አስቆመ

ዛውያህ ተብላ ከምትጠራው የጠረፍ ከተማ አቅራቢያ 147 ስደተኞችን የመታደግ ስራ በሚከናወንበት ወቅት፤ አንድ የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ አባል ጀልባ ላይ ቆሞ ይታያል — AFP

የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ኃይል ከዋና ከተማዋ ትሪፖሊ በስተምዕራብ ባካሄደው ጠንከር ያለ የአንድ ቀን ዘመቻ የጥበቃ ኃይሉ መርከቦች የ 1,074 ስደተኞችን ጉዞ ማጨናገፍ መቻላቸውን አስታውቋል፡፡

የባህር ጠረፍ ጥበቃ ኃይሉ ቃል አቀባይ የሆኑት አዩብ ቃሲም እንደሚሉት፤ ከትሪፖሊ በስተምዕራብ 45 ኪሜ ርቀት ላይ የምትገኘው የዛውያ ከተማ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች ከስምንት በላይ ስደተኞች የጫኑ ጀልባዎችን አስቁመዋል፡፡
ቃል አቀባዩ እንዳሉት፤ ስደተኞቹ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት እና ከአረብ አገሮች የመጡ ሲሆን ከሳብራታ እና አቅራቢያዋ ከሚገኙት የታሊል እና ዋዲ አካባቢዎች ተነስተው ጉዞ የጀመሩ ነበሩ፡፡

ጀልባዎቹ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ፤ ስደተኞቹ የታሰሩ ሲሆን ዛውያ ተብላ በምትጠራው የሊቢያ ከተማ ወደሚገኝ የስደተኞች ማጎርያ ካምፕ ተልከዋል፡፡
በፈረንጆቹ አቆጣጠር እስከ መስከረም 17 ባለው ሳምንት ውስጥ በአብዛኛው በሀገሪቱ ምዕራባዊ የባህር ጠረፍ አቅራቢያ ከሚገኙት የዛውያ እና ሳብራታ አካባቢዎች በተካሄዱ 12 የተለያዩ ዘመቻዎች፤ ከ 3,000 በላይ ስደተኞችን ማስቆም መቻሉን የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ኃይል በተጨማሪ አስታውቋል፡፡
ከሓምሌ ወር ጀምሮ ከሊቢያ የባህር ጠረፍ ተነስተው ወደ ኢጣሊያ የሚጓዙ ስደተኞች ቁጥር የቀነሰ ቢሆንም፤ ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ስደተኞችን ለባህር ጉዞ በማይመጥኑና ከመጠን በላይ በታጨቁ ጀልባዎች ጭነው በሜዲትራንያን ባህር ላይ መላካቸውን ቀጥለውበታል፡፡

የአውሮፓ ህብረት እና ኢጣሊያ ስደተኞች የጫኑ ጀልባዎችን ማስቆም ይችሉ ዘንድ ለሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ አባላት እገዛ ሲያደርጉላቸው ነበር፤ ነገር ግን ኢጣሊያ ስደተኞች ገና ሊቢያ ሳይደርሱ ለማገድ ፍላጎቱ አላት፡፡

ሊቢያና ኢጣሊያ መስከረም 15 በኢጣሊያው የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሚኒቲ ሊቀመንበርነት ሮም ውስጥ ባካሄዱት ስብሰባ፤ በሊቢያ ደቡባዊ ድንበር ላይ ለባህር ጠረፍ ጠባቂዎች የአቅርቦት ማዕከል ለማቋቋም እና በአካባቢው የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች የሚኖራቸውን እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡