በኢትዮጵያ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ወደ ዩንቨርሲቲዎች ገቡ

የፎቶ ምንጭ: የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፡፡ ኤርትራውያን ስደተኛ ተማሪዎች፡፡

በኢትዮጵያ የሚገኙ ወደ 450 የሚደርሱ ስደተኞች በኢትዮጵያ ዩንቨርሲቲዎች ውስጥ ገብተው መማር እንዲችሉ በፈረንጆቹ 2017 ማገባደጃ ላይ ፈቃድ አግኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር (ARRA) እንደሚለው፤ ተማሪዎቹ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ በሚገኙ 23 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበዋል፡፡

ተማሪዎቹ የኤርትራ፣ ደቡብ ሱዳን፣ የመን እና ሶማሊያ ስደተኞች ይገኙባቸዋል፡፡
ስደተኞች በኢትዮጵያ ዩንቨርሲቲዎች ገብተው እንዲማሩ የተወሰነው በፈረንጆቹ 2010 ሲሆን፤ በወቅቱ ከ 200 በላይ ኤርትራውያን ተማሪዎች በመቐለ፣ አክሱም እና አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲዎች ገብተው ለመማር ተመዝግበዋል፡፡

ይህ የከፍተኛ ትምህርት አቅርቦት ‘ከስደተኞች-ጣቢያ-ውጪ-የመኖር-ፖሊሲ’ የሚባለው አሰራር አንድ አካል ሲሆን፤ ይህም በፈረንጆቹ ነሓሴ 2010 ላይ በኢትዮጵያ መንግስት እና በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) መካከል ምክክር ከተደረገ በኋላ ነው ተግባራዊ መሆን የጀመረው፡፡ ይህ ፖሊሲ በስደተኞች ጣቢያ ይኖሩ የነበሩ ስደተኞች እራሳቸውን በገንዘብ ማገዝ እስከቻሉ ድረስ፤ በመረጡት የትኛውም የሀገሪቱ ክፍል በነፃነት መኖር እንዲችሉ የሚፈቅድ ነው፡፡

ከስደተኞች-ጣብያ-ውጪ-መኖር የሚፈቅደው መርሃግብር፤ በተጨማሪም ስደተኞች በየትኛውም የመንግስት እና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ገብተው መማር እንዲችሉ ያደርጋቸዋል፡፡
ቀደም ብለው በተሰጡ ነፃ የትምህርት ዕድሎች ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ አንዳንድ ስደተኞች ከተመረቁ በኋላ ሀገሪቱ ውስጥ ስራ ማግኘት አልቻሉም፡፡ ነገር ግን፤ በቅርቡ ይፋ የሆነው አዲስ አሰራር ስደተኞች ኢትዮጵያ ውስጥ መደበኛ የስራ ዕድል ማግኘት እንዲችሉ ድጋፍ ያደርግላቸዋል፡፡

ባለፈው ህዳር ወር፤ የኢትዮጵያ መንግስት ሁሉንአቀፍ የስደተኞች ጉዳይ አሰራር (CRRF) ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ ይህ አሰራር የስደተኞችን አካባቢያዊ ቁርኝት የሚያሻሽል፤ ለስደተኞች የሚቀርብ መሰረታዊ እና አስፈላጊ የሆኑ ማህበራዊ አገልግሎቶችን የሚያሻሽል እንዲሁም ደግሞ ስደተኞች የስራ ፈቃድ ማግኘት እንዲችሉ የሚያደርግ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ሁሉንም የስደተኞች ጣቢያዎችን ለመዝጋት እቅድ ያለው ሲሆን፤ CRRF ሀገሪቱ ውስጥ ለሚገኙ ስደተኞች ዘላቂ መፍትሄ ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡