ሜዲትራንያን ባህር ላይ ተጨማሪ ስደተኞች እየጠፉ ነው
የስደተኞች ጀልባዎች ወደ ጣልያን ለመድረስ ሲሞክሩ ሜዲትራንያን ባህር ላይ በተደረጉ ሁለት የነፍስ አድን ዘመቻዎች ቢያንስ 21 ስደተኞች መጥፋታቸውና ሁለት ሞተው መገኘታቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
ኤስ ኦ ኤስ ሜድትራኔ የተባለው ነፍስ አድን የዕርዳታ ድርጅት እንዳለው የእርዳታ ሰራተኞች የታደጓቸው አብዛኞቹ ስደተኞች ከምዕራብ አፍሪካ የመጡ ቢሆንም፤ ከሱዳንና ደቡብ ሱዳን የመጡም ይገኙባቸዋል፡፡ ከነዚህም መካከል አንዲት እርጉዝ የምትገኝባቸው ሶስት እንዲሁም ደግሞ 14 ካለ ወላጅ ወይም ጠባቂ የሚጓዙ ህፃናት ስደተኞች ይገኙባቸዋል፡፡
በፈረንጆቹ መጋቢት 6 በጣልያኗ የፖዛሎ ደሴት የደረሱት ስደተኞች መጀመርያ ነፍሳቸውን የታደጉላቸው በሰሜን አፍሪካ የባህር ጠረፍ አቅራቢያ የነበሩ ቆጵሮሳውያን የንግድ መርከብ ሰራተኞች ሲሆኑ፤ እነሱም አኳሪየስ ተብላ ለምትጠራው ኤስ ኦ ኤስ ሜድትራኔ (SOS Mediterranee) እና ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን (MSF) በጋራ ለሚያንሳቅሷት መርከብ ሰራተኞች አስረከቧቸው፡፡
ኤስ ኦ ኤስ ሜድትራኔ እንዳለው፤ ስትሰምጥ ከነበረችው የእንጨት ጀልባ በሂወት መትረፍ የቻሉት ሰላሳ ሲሆኑ፤ አንዲት ነፍሰፁር ሴትን ጨምሮ 21 ሰዎች ደግሞ መሞታቸውን፤ በሂወት መትረፍ የቻሉት ስደተኞች ተናግረዋል፡፡
“በዛች የእንጨት ጀልባ ላይ 51 ሰዎች ነበርን፡፡ ነገር ግን ሰዎች በማታ ሲፈሩና ጀልባዋም መስጠም ስትጀምር፤ ሰዎች ወደ ባህሩ ገቡ” ሲል አንድ ጋምቢያዊ ወጣት ስደተኛ ለ ኤስ ኦ ኤስ ሜድትራኔ ተናግሯል፡፡
“ጀልባዋ ላይ 5 ሴቶች ተሳፍረው ነበር፤ አንዲት እርጉዝ ሴት ጨምሮ አራቱ ሰጥጠው ሞቱ፡፡ እኔ ወንድሜን አጥቻለው፡፡” ይሏል ጋምቢያዊው ወጣት፡፡
የዓለምአቀፉ የስደት ጉዳዮች ድርጅት (IOM) ቃልአቀባይ ጆኤል ሚልማን እንዳሉት፤ በእንጨት ጀልባዋ ላይ ሁለት ህፃናት ሞተው የተገኙ ሲሆን፤ ይህም የሟቾቹን ቁጥር ወደ 23 አድርሶታል፡፡
ሌሎች 42 ስደተኞች ደግሞ የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ሃይል በቁጥጥር ስር አውሎ ወደ ሊቢያ እንዳይመልሷቸው ሲሉ ከነበሩባት የጎማ ጀልባ ላይ የዘለሉ ቢሆንም ሂወታቸውን ግን መታደግ ተችሏል፡፡ በሁለተኛው የተጓዦች ቡድን የነበሩት ሰዎች እንዳሉት፤ 90 ሰዎች በሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ኃይል ተይዘው ወደ ሊቢያ ተመልሰዋል፡፡
የአኳሪየስ መርከብ ሰራተኞች ሂወቱን የታደጉለት አንድ ስደተኛ የ 7 ዓመት ህፃን የእህቱ ልጅ በሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ሃይል ጀልባ ተጭና ወደ ሊቢያ ከመወሰዷ በፊት “አጎቴ ትተሀኝ አትሂድ” ስትለው መስማቱን ለ MSF ተናግሯል፡፡
“ይህ እንዴት እንደተከሰተ ባናውቅም ነገር ግን የቤተሰብ አባላት ተለያይተዋል፤ እኛ ደግሞ ዳግም እንዴት ልናገናኛቸው እንደምንችል እያሰብንበት ነው” ሲሉ በጣሊያን የአይኦኤም ቃልአቀባይ የሆኑት ፍላቭዮ ዲ ጂያኮሞ ለ AFP ተናግረዋል፡፡
ሊቢያ ኦብዘርቨር የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው፤ የዙዋራ ከተማ የፀጥታው ክፍል በሊቢያና በቱኒዝያ ድንበር አቅራቢያ ከዙዋራ 40 ኪሎሜትር በስተምዕራብ ርቃ በምትገኘው ፋርዋ ደሴት አቅራቢያ 97 ስደተኞች መታደጋቸውን ይፋ አድርጓል፡፡ ስደተኞቹ ወደ ዙዋራ የተወሰዱ ሲሆን ቆየት ብሎ ደግሞ በከተማዋ ለሚገኙ የስደተኞች ጉዳይ ለሚመለከታቸው ባለስልጣናት ተላልፈዋል፡፡
ኤስኦኤስ ሜድትራኔ እንደገለፀው፤ የአኳሪየስ መርከብ ሰራተኞች የመታደግ ስራቸውን በሚያከናውኑበት ግዜ የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ሃይል የቅኝት ጀልባ ተጠግታቸው ነበር፡፡ ጀልባዋ የመጣቸው በከፍተኛ ፍጥነት ሲሆን ከአኳሪየስ የተደረገውን የመገናኛ ሬድዮ ጥሪም አልመለሰችም፡፡ የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ኃይል ቆይቶ እንዳስታወቀው የነፍስ አድን ዘመቻውን ለመተባበር አስቦ ያደረገው ነገር እንደሆነ ገልጿል፡፡
የኤስኦኤስ ሜድትራኔ የነፍስ አድን ዘመቻ አስተባባሪ የሆኑት ኖኮላ ስታላ “የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ሃይል አባላት አደገኛና ህገወጥ ባህሪ የዚህ ባህር አደገኛነትን በድጋሚ የሚያሳይ ነው፤ ይህ ባህር ቀድሞዉንም ቢሆን ከዓለማችን እጅግ አደገኛው ነው” ብለዋል፡፡
በ 2018 የመጀመርያዎቹ ዘጠኝ ሳምንታት ቢያንስ 421 ስደተኞች በሜዲትራንያን ባህር ሞተው ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ