የሜዲትራንያን ነፍስ አድን ቡድኖች ስራ አቆሙ

ስደተኞች በዚህ ወር ውስጥ ከሊቢያ ጠረፍ የሜዲትራንያን ባህር ላይ የ SOS Mediterranee እና ድንበር የለሽ ዶክተሮች መርከብ እንድትታደጋቸው በመጠባበቅ ላይ፡፡ የፎቶ ምንጭ አንጄሎስ ዞርተዚንስ / አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ – ጌቲ ኢሜጅስ

የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ሃይል ስጋት አሳድሮብናል በማለት ሶስት የዕርዳታ ቡድኖች በሜዲትራንያን የሚያከናውኑት ስደተኞችን የመታደግ ስራ አቁመዋል፡፡
ድንበር የለሽ ሃኪሞች (Medecins Sans Frontieres)፣ ሴቭ ዘ ችልድረን እና የጀርመኑ ሲ አይ የተሰኙት ድርጅቶች የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ሃይል በያዘው ሞገደኛ አቋም ምክንያት ሰራተኞቻቸው ስራቸውን ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ ማከናወን እንዳልቻሉ በይፋ አሳውቀዋል፡፡
ሁኔታውን አስመልክተው አስተያየታቸውን የሰጡት የኢጣሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንጀሊኖ አልፋኖ እንዳሉት፤ እየጨመረ የመጣው የሊቢያ ሚና በሜዲትራንያን ባህር ላይ የነበረውን የአቀባበል ሁኔታ ላይ “ማስተካከያ” ፈጥሯል ያሉ ሲሆን፤ በተጨማሪም የዕርዳታ ድርጅቶቹ ስደተኞችን የመታደግ ተግባራቸውን ለማቆም የወሰኑት ውሳኔም የዚሁ አዎንታዊ ሂደት አካል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ሃይል ጀልባዎችና በዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶች መርከቦች መካከል በሊቢያ የውሃ ግዛቶች ጠረፍ አካባቢ ግጭት መከሰቱ በተደጋጋሚ የተነገረ ቢሆንም፤ የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ሃይል ግን የሂወት አድን ተግባራቱን ለመቆጣጠር ብቻ እየሰራ እንደነበር ይናገራል፡፡
የባህር ጠረፍ ጥበቃ ሃይሉ ቃል አቀባይ የሆኑት ጄኔራል አዩብ ቃሲም እንዲህ ብለዋል: “ባጠቃላይ፤ እኛ የዕርዳታ ድርጅቶቹን መኖር አንቃወምም፤ ነገር ግን ከሊቢያ መንግስት ጋር ይበልጥ ተባብረው እንዲሰሩ እንፈልጋለን፡፡ ለሊቢያ ሉዓላዊነት ይበልጥ ክብር ማሳየት ይኖርባቸዋል፡፡”
የዕርዳታ ድርጅቶቹ የሚያንቀሳቅሷቸው መርከቦች የስደተኞችን ሂወት ሲታደጉ ነበር፤ እንዲያ ባይሆን ኑሮ ስደተኞቹ ሜዲትራንያን ላይ ሰምጠው ሂወታቸው ያልፍ ነበር፡፡ ነገር ግን፤ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች በሜዲትራንያን በኩል ለባህር ጉዞ ብቁ ባልሆኑና ከአቅም በላይ የጫኑ ጀልባዎችን በመጠቀም ብዙ ሰዎችን እንዲልኩ የእርዳታ ድርጅቶቹ እያበረታቱ ነው ሲሉ የሊቢያና የኢጣሊያ መንግስታት ይወቅሷቸዋል፡፡
የኢጣሊያ መንግስት በቅርቡ ጥብቅ የሆነ የስነምግባር ደንብ አቅርቧል፤ ደንቡም ሂወት የመታደግ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ቡድኖች ስራዎቻቸውን እንዴት ማከናወን እንዳለባቸው የሚደነግግ ነው፤ ከዚሁ ጎን ለጎን በደቡባዊቷ የጣሊያን ግዛት ሲሲሊ ውስጥ የሚገኙ አቃቤህጎች ከህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ጋር ተባብረዋል ያልዋቸው አንዳንድ የዕርዳታ ድርጅቶች ላይ ምርመራ እያደረጉ ነው፡፡