ብዙ ስደተኞች  ወደ ስፔን ለመድረስ ሲሉ ሂወታቸውን ለአደጋ እያጋለጡ ነው

ነሓሴ 9 ላይ በስፔን ደቡባዊ ጠረፍ በሚገኝ የባህር ዳርቻ ሲዝናኑ በነበሩ ጎብኚዎች የተቀረፀ አንድ ምስል፤ ብዙ ስደተኞች በፕላስቲክ ጀልባ ተጭነው ድንገት የባህር ዳርቻው ላይ ሲደርሱ ያሳያል፡፡

ከሰሜን አፍሪካ የባህር ጠረፍ 12 ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ በደቡብ ስፔን ውስጥ በምትገኘው የካዲዝ ግዛት ውስጥ፤ ባህር ዳርቻ ላይ ፀሃይ በመሞቅ እየተዝናኑ የነበሩት ጎብኚዎች፤ 30 ያክል ስደተኞችን የጫነች አንዲት የፕላስቲክ ጀልባ ድንገት ዳርቻው ላይ ስትደርስ ተገርመዋል፡፡ ተጓዦቹ ወዲያው ወደ የብሱ ሮጠው ከወጡ በኋላ ተሰውረዋል፡፡

AFP የዜና ምንጭ እንደዘገበው፤ ባህር ዳርቻው ላይ ከደረሱት 30 ያክል ስደተኞች፤ የስፔን ባለስልጣናት ቆየት ብሎ ዘጠኙን ማግኘት ችለዋል፡፡ ሁሉም በአፍላ የዕድሜ ደረጃ ላይ የሚገኙ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች ሲሆኑ፤ ከሞሮኮ የመጡ ናቸው ተብሎ ተገምቷል፡፡ ወደ ስደተኞች መቀበያ ማዕከላት እንዲገቡ የሚገባቸው ሆነው ተገኝተዋል፡፡

ዓለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት (IOM) እንዳለው፤ በያዝነው ዓመት እስካሁን ድረስ ብቻ 11,849 ስደተኞች ወደ ስፔን የገቡ ሲሆን፤ በ 2016 ግን ዓመቱን ሙሉ የነበረው የስደተኞች ቁጥር 13,246 ነበር፡፡

“ይህ ለውጥ የተከሰተው፤ ወደ [ስፔን] የሚወስደው መንገድ በሞሮኮ በኩል እስከ ጠረፉ ድረስ አደጋ የሌለበት የጉዞ መስመር ተብሎ ስለታሰበ ነው ብለን እናምናለን” ብለዋል የ IOM ቃል አቀባይ ዮኤል ሚልማን፡፡
የ IOM ዋና ቃል አቀባይ ፍላቪዮ ዲ ጂያኮሞ፤ ስደተኞች ሊቢያ ውስጥ እየተባባሰ ያለውን ሁኔታ ከሰሙ በኋላ የጉዞ መስመራቸውን እየቀየሩ ሊሆን ይችላል የሚል ሃሳብ ሰንዝረዋል፡፡

“ቀደም ብሎ ብዙ የስደተኞች ፍሰት ባስተናገድንበት ጥር ወር ላይ፤ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎቹ የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ የስደተኞችን ጀልባ በቅርቡ ማስቆም ይጀምራል ብለው ለስደተኞቹ ስለነገርዋቸው በብዛት ወደ ስፔን መምጣታቸውን ተናግረው ነበር፡፡ ስለዚህም፤ በደንብ መረጃው አላቸው፡፡” ብለዋል ዲ ጂያኮሞ፡፡

በሞሮኮ በኩል ወደ ሊቢያ የሚጓዙት ስደተኞች አብዛኞቹ ከሴኔጋል፣ ጋምቢያ፣ ጊኒ እና ኣይቮሪኮስትን ጨምሮ ከምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የሚመጡ ናቸው፡፡

ሊቢያ በህገወጥ የሰው አዘዋዋሪ ጀልባዎች ላይ በቅርቡ መውሰድ የጀመረችውን እርምጃ ተከትሎ፤ ወደ ስፔን የስደተኞች ፍሰት እየጨመረ ባለበት በዚህ ወቅት፤ ድንበር ዘለል የሃኪሞች ቡድን በመባል የሚታወቀው Médecins Sans Frontières (MSF) ን ጨምሮ የሰብዓዊ መብት ተሟጓች ቡድኖች፤ የስፔን የስደተኞች መቀበያ ማዕከላት ከአቅማቸው በላይ መጨናነቃቸውንና አዳዲስ ስደተኞችን እያስተናገዱ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ወር ይፋ የሆነው የሂዩማን ራይትስ ዎች ሪፖርት፤ በባህር ወደ ስፔን የሚገቡ ጥገኘነት ጠያቂዎቸና ሌሎች ስደተኞች አብዛኛውን ግዜ ጥሩ ባልሆነ አያያዝ ስር እንደሚቆዩና የጥገኝነት ጥያቄ ለማቅረብ እንቅፋቶች እንደሚገጥሟቸው አመልክቷል፡፡ ፖሊስ ጣቢያዎች ውስጥ በሚገኙ የእስር ክፍሎች ላይ ለቀናት ይታሰራሉ፤ እንዲሁም ደግሞ ወደሃገራቸው ተመልሰው እስኪላኩ ድረስ በስደት ጉዳዮች ማቆያ ተቋማት ውስጥ ለረጅም-ጊዜ ይታሰራሉ፡፡