የስፔን ፖሊስ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪ ቡድን በቁጥጥር ስር አዋለ

የስፔን ፖሊስ፤ ከሞሮኮ በጂብራልተር መተላለፍያ በኩል ፈጣን የሞተር ጀልባዎችን በመጠቀም ስደተኞችን በህገወጥ መንገድ ሲያሻግር የነበረን አንድ ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ቡድን በቁጥጥር ስር አውሏል፡፡

ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎቹ ከሞሮኮ ተነስተው ደቡባዊ ስፔን ውስጥ ወደሚገኙት የማጋላ እና ካዲዝ ግዛቶች በየቀኑ ጉዞ ያደርጉ ነበር፡፡ በእያንዳንዱ ጉዞም ስደተኞች እያንዳንዳቸው እስከ 5,000 ዩሮ የሚደርስ ገንዘብ የሚከፍሉ ሲሆን ከዚያም አስር-ደቂቃ ብቻ በሚፈጀው የጂብራልተር መተላለፍያ ለማቋረጥ በፈጣን የሞተር ጀልባዎች ይጓጓዛሉ፡፡

ስፔን እንደደረሱም ስደተኞቹ በደቡባቷ የወደብ ከተማ አልጀሲራስ ውስጥ ወደሚገኝ የማቆያ ስፍራ ይወሰዳሉ፤ እዚያም የስደተኞቹ ዘመዶች ለህገወጥ የሰው አዘዋዋሪው ክፍያ መፈፀማቸው እስኪረጋገጥ ድረስ ለብዙ ሰዓታት እንዲቆዩ ይደረጋል፡፡
የስፔን ፖሊስ ቃል አቀባይ እንዲህ ብለዋል፡ “የስደተኞቹን ሂወት አደጋ ላይ ሲጥሉ ነበር እንዲሁም ደግሞ አንዳንዶቹ አለታማ ቦታዎች ላይ ተጋጭተው በሚያርፉበት ወቅት አንዳንድ ጉዳቶች ደርሶባቸዋል፡፡”

አንድ ህገወጥ የሰዎች አዘዋወሪ ቡድኑ አባል እና ሁለት ስደተኞች  አልጀሲራስ ውስጥ የታሰሩ ሲሆን፤ ሌሎች ሁለት የቡድኑ አባላት ደግሞ ሰሜን አፍሪካ ውስጥ በሚገኝ ሴውታ የተባለ የስፔን ልዩ ይዞታ ላይ በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
ሶስቱ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች በህገወጥ የሰዎች ዝውውር እና ጠለፋ የወንጀል ድርጊቶች ክስ የቀረበባቸው ሲሆን፤ ያመለጡት ሁለቱ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ደግሞ በአሁኑ ሰዓት ዓለምአቀፍ የእስር ማዘዣ ተቆርጦባቸዋል፡፡

ስደተኞች በሊቢያ እየተባባሰ የመጣውን ሁኔታ ለማስወገድ ሲሉ፤ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ደግሞ የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ሃይል በቅርቡ በማድረስ ላይ ያለውን ጥቃት ለማምለጥ በሚሞክሩበት በአሁኑ ወቅት፤ ወደ ኢጣሊያ የሚደርሱ ስደተኞች ቁጥር ሲያሽቆለቁል ወደ ስፔን የሚደርሱ ስደተኞች ቁጥር ግን በፍጥነት ጨምሯል፡፡
ከአውሮፓ ህብረት የድንበር እና የባህር ጠረፍ ጥበቃ ኤጀንሲ (Frontex) የተገኘ አዲስ አሀዝ እንደሚያመለክተው፤ ሓምሌ ወር ውስጥ ወደ ኢጣሊያ የደረሱ ስደተኞች ቁጥር በ 57% ቀንሷል፡፡

“በሓምሌ ወር የመጀመርያዎቹ ቀናት በባህሩ ላይ የነበረው ከባድ የአየር ሁኔታን ጨምሮ፤ በቅርብ ሳምንታት በመካከለኛው የሜዲትራንያን የሚደረገውን የስደተኞች ጉዞ እንዲቀንስ አስተዋፅኦ ያደረጉ ብዙ ምክንያቶች አሉ” ብሏል Frontex፡፡

“በሊቢያ የጉዞ መነሻ ቁልፍ ቦታ በሆነችው ሳብራታህ አቅራቢያ ግጭቶች መኖራቸው፤ እዚያ ያለውን ስደተኞችን የማዘዋወር ስራ ከባድ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በተጨማሪም፤ የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ የሚያደርገውን ቁጥጥር ከፍ በማድረጉም ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎቹ ስደተኞችን የጫኑ ጀልባዎችን እንዳይልኩ አድርጓቸዋል” በማለት Frontex አክሏል፡፡