የግብፅ ባህር ጠረፍ ጠባቂዎች 40 ሕገ ወጥ ስደተኞችን አሰረ

ስእል፡ ሻተርስቶክ፡ የግብፅ የባህር ጠረፍ እየተዘዋወረ የሚጠብቅ ጃልባ

ባለፈው ሕዳር ወር የመጀመርያው ሳምንት ላይ የግብፅ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች ከምሥራዊ ካይሮ ወደ አለክሳንድርያ በመጓዝ የሜዲቴራንያን ባህርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመሻገር ያሰቡት 40 ስደተኞችን በመያዝ ጉዞኣቸው እንዲቋረጥ አድርገዋል፡፡
በየቀኑ ከሚወጣው የግብፅ ጋዜጣ (ኢጂፕት ቱደይ) ሪፖርት መሰረት ግብፅን አቋርጠው እንዲያሸጋግሯቸው ለአሸጋጋሪዎች ገንዘብ ከፍለናል ብለው የተናገሩት ስደተኞች ወዲያዉኑ ታስረው ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡
በጥቅምት ወር የግብፁ ፓርላማ ሕገ-ወጥ ስደትንና አስተላላፊዎችን የሚመለከት በዚሁ ሥራ ለተገኙትም እጅግ በጣም ከባድ ቅጣት የሚያስከትል አዲስ ሕግ አወጣ፡፡
የወጣው ሕግ ዓላማ አሸጋጋሪዎች ስደተኞች ከግብፅ እንዳያሸጋግሩ ተስፋ የሚያስቆርጥና፣ ስደተኞችን በማጓጓዝ ላይ ለሞትና ለአካል መጉደል ተጠያቂ የሆኑትን ለከባድና ረጅም ቀናት እስር እንደሚዳረጉ ነው፡፡ በተጨማሪም ሕጉ ሴቶችና ሕፃናትን የሚያስተላልፉና ለስደተኞች በማስመሰል የሚሠራ አዲስ የማንነት መታወቂያ የሚያዘጋጅቱንም ክፉኛ እንደሚቀጣ ያትታል፡፡
ይህ ስለ ሕገ-ወጥ ስደተኞችና አስተላላፊዎች መጥፎ ሥራ የመቅረፍ ጥረት የተጀመረው ባለፈው ዓመት መስከረም ወር ላይ በበሀይራ ግዛት በራሺድ ጠረፍ ከ200 ስደተኞች በላይ አሳፍራ በሰው ብዛት ምክንያት የተገለበጠችው ጀልባ ከተከሰተው አደጋ በኋላ ነው፡፡

ግብፅ ሕገ-ወጥ ስደትን ለመቋቋም ከጣልያን መንግሥትና ከአውሮፓ ኅብረት ጋር በመሥራት ላይ ትገኛለች፡፡ በግብፅና በጣልያን መንግሥት መካከል በተደረገው የፕሮቶኮል ትብብር መሠረት በመስከረም ወር ላይ ለግብፅ የፖሊስ አካዳሚ የፖሊስ የምርምር ማእከል ከ22 የአፍሪቃ አገሮች ለተውጣጡት ለ360 ከፍተኛ የፖሊስ አባሎች፣ በሕገ-ወጥ ስደትንና የተደራጀ ወንጀል መዋጋትን በሚመለከት ሥልጠና ተከፍቷል፡፡
በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት (UNHCR)፣ መሰረት ከግብፅ ለመውጣት በመሞከር ላይ እያሉ የታሰሩት ሕገ-ወጥ ስደተኞች ቁጥር ያለፋታ እየጨመረ ነው፡፡ በ2016 የኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ሶማሊያ ዜጎች ከግብፁ ሰሜናዊ ጠረፍ ለመውጣት በመሞከር ላይ የነበሩት በግብፅ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች 4,600 ሰዎችን መታሰራቸው ሪፖርቱ ይገልፃል፡፡