ሆላንድ ወደ እንግሊዝ ድንበርዋን ሲያቋረጡ የነበሩ ስደተኞች ያዘች
ሆላንድ ወደቦችዋን ተጠቅመዉ ወደ እንግሊዝ ይጓዙ የነበሩ ህገወጥ ስደተኞች በቁጥጥር ስር መዋሏ በድንበር አካባቢ
የምታደርገዉ ጥበቃና ክትትል ማጠናከሯ አንድ ማሳያ ሆኖዋል።
ባለፈዉ 3 ወራት የሆላንድና የእንግሊዝ የድንበር ጥበቃ ባለስልጣናት በከባድ መኪኖችና ጀልባዎች ይጓዙ የነበሩ 430
ህገወጥ ስደተኞችን በቁጥጥር ስር አዉለዋል፡፡ በ2015 ዓ.ም በቁጥጥር ስር ከዋሉት 500 ህገወጥ ስደተኞች ከእጥፍ
በላይ ባለፈዉ ዓመት 1280 ህገወጥ ስደተኞች ከሆላንድ ሲነሱ በቁጥጥር መዋላቸዉም ተዘግቧል፡፡
በ2015 መገባደጃ የእንግሊዝ መንግስት ህገወጥ ስደትን ለመከላከል ከቤልጄየምና ሆላንድ መንግስታት ጋር ስምምነት
ተፈራርሟል፡፡ ይህ ስምምነት ሦስቱም መንግስታት መረጃን በመለዋወጥ፣ በመነሻ ወደቦቻቸዉ ጥበቃና ቁጥጥር
ለማድረግ አዳዲስ የመዘዋወርያ መስመሮችን በመለየትና በማወቅ በህገወጥ የሰዉ ንግድ ማዘዋወር ላይ የተሰማሩ
ወንጀለኞችን ለመወጋት የሚያስችል ነዉ፡፡ በዚህም መሠረት የሆላንድና የእንግሊዝ የድንበር ጥበቃ ሃይሎች በመነሻ
ወደቦቻቸዉ ላይ ጥበቃቸዉና ክትትላቸዉ በማጠናከር ህገወጥ ስደትን ለመከላከል መነሳታቸዉ ተዘግቧል፡፡
በሰኔ 2016 የሆላንድ መንግስት የድንበር ላይ ጥበቃን ለማገዝ የታጠቀ ሰራዊት ወደ ሮተርዳምና ጁምይደን
በማንቀሳቀስ ወደ ሃርዊች፣ ሁልና ኒዉካስትል ወደቦች የሚደረጉ ህገወጥ ስደት ላይ ጥበቃዉ ማጠናከሩ የተዘገበ
ሲሆን ድንበር በሚያቋርጡ ከባድ መኪኖች ላይ አነፍናፊ ዉሾችን በመጠቀም ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ላይ
ይገኛል፡፡ በተመሳሳይ የእንግሊዝ መንግስት በምስራቅና ደቡብ የድንበር ወደቦቿ ላይ ጠባቂ ሃይሏን በእጥፍ ጨምራለች፡፡
የከባድ መኪና ሹፌሮች ህገወጥ ስደተኛ ደብቀዉ ከተገኙ እስከ 2500 ዩሮ ቅጣት እንደሚጣልባቸዉና ይህም
እነሱ ሳያዩዋቸዉ ተደብቀዉ ቢገኙም ከቅጣቱ እንደማያመልጡ ተገልጿል ፡፡ በዚህም መሰረት የከባድ መኪና ሹፌሮች
ህገወጥ ስደተኞች በብዛት የሚገኙባቸዉ መንገዶችን መጠቀም ማቆም መጀመራቸዉ ተዘግቧል፡፡
በ2015 የሆላንድ መንግስት ድንበሮቹን አቋርጠዉ ወደ እንግሊዝ ከሚጓዙ ህገወጥ ስደተኞች 55% በቁጥጥር
ስር ያወለ ሲሆን ይህ ቁጥር በ2016 ወደ 83% አድጓል፡፡ በ2016 በቁጥጥር ስር የዋሉ ህገወጥ የሠዎች ዝዉዉር
ነጋዴዎች ቁጥር መጨመሩም ተዘግቧል፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ