የቀኝ አክራሪ ኃይሎች፤ ስደተኞችን ከባህር የመታደግ ስራ ለማስቆም ሙከራ አደረጉ

ባለፈው ወር፤ የኢጣሊያዋ ደሴት ሲሲሊ ከንቲባ አንድ የቀኝ አክራሪ ቡድን የተከራየውን መርከብ በወደባቸው መጠቀም እንዳይችል ሊያግዱ ተነሳስተዋል፡፡ መርከቧን የተከራያት ጄኔሬሽን አይደንቲቲ የሚባል ፀረ-እስልምናና ፀረ-ስደተኞች ሃሳብ አራማጅ የሆኑ ከመላው አውሮፓ የተውጣጡ ወጣቶች የተሰባሰቡበት ቡድን ሲሆን፤ ፍላጎቱም ስደተኞች ከሊቢያ ወደ አውሮፓ እንዳይገቡ መከልከል ነው፡፡

የዚህ ሃሳብ አራማጆች “አውሮፓን እንከላከልላት” የተሰኘ ዕቅዳቸው አንድ አካል በማድረግ፤ ከብዙ ሰዎች ገንዘብ በማሰባሰብ ጅቡቲ ውስጥ መርከብ ተከራይተዋል፡፡ ሰኔ ወር ላይ በተደረገ “የሙከራ እንስቃሴ” ቡድኑ በተሳካ ሁኔታ በአንድ የዕርዳታ ድርጅት ሊከናወን የነበረውን ስደተኞችን ከሲሲሊ የባህር ጠረፍ ላይ የመታደግ ዘመቻ ማስተጓጎሉን ተናግሯል፡፡

የዚህ እንቅስቃሴ አራማጆች እንደሚሉት ዓላማቸው “ወንጀለኛ” ብለው በሚጠሯቸው የዕርዳታ ድርጅቶች አሳሽ እና ነፍስ አድን ጀልባዎች የሚፈፀሙ አግባብ ያልሆኑ ተግባራትን ማጋለጥ ነው፤ የዕርዳታ ድርጅቶቹ ስደተኞችን ወደ አውሮፓ በህገወጥ መንገድ ከሚያሻግሩና ከሚያጓጉዙ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ጋር አብረው ይሰራሉ ሲሉ ይከሷቸዋል፡፡ የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ኃይል በመጥራት ሜዲትራንያንን ለማቋረጥ የሚሞክሩትን ስደተኞች መልሰው ወደ ሊቢያ እንዲወስዷቸው በማድረግ የነፍስ አድን ሰራተኞችን እንቅስቃሴ ለማወክም ዕቅድ ይዘዋል፡፡

በያዝነው ዓመት ብቻ፤ ከ 2,400 በላይ ስደተኞች ሜዲትራንያንን አቋርጠው ከሊቢያ ወደ ኢጣሊያ ለመግባት ሲሞክሩ ሂወታቸውን አጥተዋል፡፡ ብዙ ስደተኞች ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ የባህር ጉዞ ለማድረግ ብቁ ባልሆኑ ደካማ ጀልባዎች ታጭቀው ነው የሚጫኑት፡፡