ስደተኞችን በህገወጥ መንገድ የምታሸጋግር መኪና በሊቢያ በመጋጨቷ 19 ሰዎች ሞቱ

ስደተኞችን በህገወጥ መንገድ ስታዘዋውር የነበረች መኪና ከሊቢያዋ ከተማ ባኒ ዋሊድ በስተደቡብ ምዕራብ 60 ኪሎሜትሮች ራቅ ብሎ በመጋጨቷ 19 ስደተኞች ሲሞቱ ሌሎች በርካቶች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸቸዋል፡፡

ዓለምአቀፉ የስደት ጉዳዮች ኤጀንሲ (IOM) እንዳለው፤ ከሟቾቹ መካከል አራት ህፃናት ይገኙባቸዋል፡፡

የተለያዩ ዘገባዎች መኪናዋ ላይ ተሳፍረው የነበሩትን ስደተኞች ቁጥር ከ 180 እስከ 300 ባለው አስቀምጠውታል፡፡ አብዛኞቹ ኤርትራውያን፣ ሶማሊያውያን ኢትዮጵያውያን ዜግነት ያላቸው እነዚሁ ስደተኞች ከሊቢያዋ ዋና ከተማ ትሪፖሊ በስተደቡብ ምስራቅ 40 ማይሎች ርቀት ላይ ወደምትገኘው ታርሁና እየተጓጓዙ ነበር፡፡

“ይህች ከመጠን በላይ በሰዎች የታጨቀችው የሰው አዘዋዋሪዎች መኪና የተጋጨችው መንገዱ ላይ አንድ ትልቅ ጉድጓድ ውስጥ ስትገባ ሚዛንዋን ስለሳተች ነው” ብለዋል መኪናዋ ላይ ተሳፍረው የነበሩት ስደተኞች ሲናገሩ፡፡

የባኒዋሊድ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ የሆኑት መሓመድ አል መብሩክ እንዳሉት ቢያንስ 78 ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ስምንቱ ከባድ ጉዳት አጋጥሟቸዋል፡፡ “ሹፌሩ እዚህ (ሆስፒታሉ) አልመጣም፤ ምን እንደገጠመውም አናውቅም” ያሉት መብሩክ “ሊሆን የሚችለው እርሱ ከአደጋው ተርፏል፤ ባይሆን ግን እዚህ ያመጡት ነበር” ብለዋል፡፡

አደጋው ከገጠማቸው ስደተኞች አብዛኞቹ በህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎቹ ወዳልታወቀ ስፍራ ተወስደዋል ተብሏል፡፡

ባኒዋሊድ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች መናሃርያ እና ጣሊያን ለመድረስ የሜዲትራንያን ባህርን የሚያቋርጡ ስደተኞች የሚተላለፉባት ከተማ ነች፡፡

ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ስደተኞችን ከጎረቤት ሀገራት ወደ ሊቢያ የሜዲትራንያን ባህር ዳርቻ አቅራቢያ በመኪና አጓጉዘው ያስገባሉ፤ እዚያም ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ይታጎራሉ አልያም ይጓጓዛሉ፤ እንዲሁም ደግሞ ለጉዞው የተለያዩ ደረጃዎች ክፍያ የሚቀበሉና ከስደተኞች አስገድደው ብር በሚቀበሉ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች እጅ ከአንዱ ወደ አንዱ እንዲንገላቱ ይደረጋል፡፡