ብዙ ስደተኞች በሊቢያ የባህር ጠረፍ አቅራቢያ ጠፉ

ሰባት ህፃናት የሚገኙባቸው 40 የሚሆኑ ስደተኞች በሊቢያ የባህር ጠረፍ አቅራቢያ የጎማ ጀልባቸው ስትሰምጥ አብረው ሰምጠው እንደሚሆን ተገምቷል። እስካሁን የአንዲት ሴት ሬሳ ተገኝቷል።

“ጀልባዋ ከጋራቡሊ ሰሜናዊ ምዕራብ አቅጣጫ አስር ኪሎሜትሮች ራቅ ብላ ነው የሰጠመችው፤ ሂወት በመታደጉ ተግባር ላይም 10 የዓሳ አጥማጅ ጀልባዎች ተሳትፈዋል” ብለዋል የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ቃል አቀባይ ጄኔራል አዩብ ቃሲም። በነዚህ የዓሳ አጥማጅ ጀልባዎችም ወደ 85 የሚጠጉ ስደተኞች ሂወት መታደግ ተችሏል።

“የዓሳ ኣጥማጆቹ ጀልባዎች እነዚህን ስደተኞች ያገኙት ከትሪፖሊ 60 ኪሎሜትሮች ወደ ምስራቅ አቅጣጫ ራቅ ካለው የጋራቡሊ የባህር ጠረፍ አቅራቢያ ነው። በጎማ ጀልባዋ ላይ ከነበረው ከባድ ጭነት የተነሳ ከእንጨት የተሰራው የጀልባው ስር በመሰበሩ መስመጥ ጀመረች” ሲሉ የአካባቢው የባህር ጠረፍ ጥበቃ መኮንን ገልፀዋል።

ከመካከላቸው 18 ሴቶች የሚገኙባቸው እነዚህ ስደተኞች አብዛኞቹ ከናይጄርያ፣ ሴኔጋል፣ ካሜሮን፣ አይቮሪ ኮስት እና ጋና የመጡ ናቸው።

ከናይጄርያ የመጣችው ቪቪያን ኤፎውሳ አብረዋት ሲጓዙ የነበሩት ተጓዦች ወደ ባህሩ ሲወድቁ እንዴት እንዳየች ታብራራለች።

“የገባንበት ጀልባ ውሃ እያሰረገ ነበር። በድንገት… ውሃ ወደ ውስጥ መግባት ጀመረ። ሁሉም ሰው መጮህ ጀመረ። ቀስ በቀስ እራሳችንን ባህሩ ላይ አገኘነው።

“አንዱ ሌላኛውን ይጎትተዋል። እንደውም እኔንም በፀጉሬ ጎትተው፤ ወደ ታች ሲስቡኝ ነበር። ስለ እውነት፤ ባህሩ ይሄን ያህል ትልቅ አይመስለኝም ነበር” ትላለች ኤፎውሳ፤ ጉዞው የሚያመጣባትን መዘዝ ቀድማ ብታውቅ ኖሮ ከናይጄርያ እንደማትወጣም ታክላለች።