አውሮፓ የሚደርሱ ስደተኞች ቁጥር ቢቀንስም ሞት እና ጥቃት ግን ጨምሯል
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) ያወጣው አዲስ ሪፖርት እንደሚያመለክተው ወደ አውሮፓ የሚደርሱ ስደተኞች ቁጥር ቢቀንስም፤ በጉዞው ላይ ሂወታቸውን የሚያጡ ስደተኞች ቁጥር ግን አሻቅቧል፡፡
እስካሁን ባለው ሁኔታ በ 2017 በባህር ተጉዞው ወደ አውሮፓ የደረሱ ስደተኞች አጠቃላይ ቁጥር፤ 2016 የመጀመርያው አጋማሽ ላይ ከነበረው ቁጥር ጋር ሲነፃፀር ቀንሷል፤ ይህም ሊሆን የቻለው በአብዛኛው የኤጂያን የጉዞ መስመር በመዘጋቱና ከቱርክ ወደ ግሪክ የሚደርሱ ስደተኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሱ ነው፡፡
በመካከለኛው ሜዲትራንያን የጉዞ መስመር፤ ከ 2016 የመጀመርያዎቹ ስድስት ወራት ጋር ሲነፃፀር የዚህ ዓመት የስደተኞች ፍሰት ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ነገር ግን፤ ከሓምሌ ወር ጀምሮ ወደ አውሮፓ የሚደርሱ ስደተኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል፡፡
ከሊቢያ ተነስተው ወደ ኢጣሊያ መድረስ የቻሉት ስደተኞች፤ አደገኛ በረሃዎችን እንዲሁም ደግሞ ፆታዊ ጥቃትን፣ ታፍኖ መወሰድን፣ ግርፋት እና ሊቢያ ላይ መታሰርን ጨምሮ በብዙ ጥቃቶች አልፈዋል ብሏል ሪፖርቱ፡፡ በባህር ወደ ኢጣሊያ በሚደረገው ጉዞ ላይ ከ 39 ሰዎች አንዱ የሞት አደጋ ይገጥመዋል፡፡
ሪፖርቱ እንደሚለው፤ በዚህ ዓመት በግንቦት ወር 686 ያክል ሰዎች በሊቢያና ኢጣሊያ መካከል በጉዞ ላይ እንዳሉ የሞቱ ሲሆን፤ በሰኔ ወር ደግሞ 300 ያክል ስደተኞች ሞተዋል ተብሎ ይገመታል፤ ይህ ደግሞ እስካሁን ድረስ በዚህ ዓመት በአጠቃላይ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ቢያንስ 2,171 ያደርገዋል፡፡
ብዙ ሰዎች ጉዞውን የሚያደርጉት በድብቅ በመሆኑ፤ የሟቾቹን ቁጥር የሚመለከት መረጃ ለማረጋገጥ ከባድ ቢሆንም በእውን ቁጥሩ ከዚህም ከፍ ያለ ነው ተብሎ ይገመታል፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ