ከ 2014 ጀምሮ ከ 1,200 በላይ ህፃናት ስደተኞች መሞታቸው ተመዝግቧል – ትክክለኛው ቁጥር ግን ከዚህ እንደሚልቅ ይገመታል

የፎቶ ምንጭ: IOM / አንድ አፍሪካዊ ህፃን ከሜዲትራንያን ባህር የነፍስ አድን ሰራተኞች ሲታደጉት ይታያል፡፡
ዓለምአቀፉ የስደት ጉዳዮች ድርጅት (IOM) ከፈረንጆቹ 2014 ጀምሮ ከ 1,200 በላይ ስደተኛ ህፃናት መሞታቸውን የመዘገበ ሲሆን፤ ከነዚህም ግማሽ ያህሉ ሜዲትራንያን ባህርን ለማቋረጥ ሲሞክሩ ነው የሞቱት፡፡

IOM እንዳለው፤ የዚህ አደጋ ትክክለኛው መጠን በልክ አይታወቅም ምክንያቱም የመረጃ አያያዝ እጥረት ስላለ፡፡

“ትክክለኛው ቁጥር ከዚህ ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል፤ ከአጠቃላይ ስደተኞች 12.5 በመቶ የሚሆኑት ከ 18 ዓመት በታች መሆናቸውን ታሳቢ በማድረግ፤ እንዲሁም ደግሞ በመላው ዓለም የሚሰደዱ ህፃናት ቁጥር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየጨመረ መጥቷል” ሲል IOM በቅርቡ በለቀቀው የሚድያ መግለጫ ላይ አስፍሯል፡፡ “ለምሳሌ፤ በፈረንጆቹ 2015 ባህር አቋርጠው ወደ ኢጣሊያ እና ግሪክ ከገቡት አንድ ሚልዮን ከሚሆኑት ስደተኞች መካከል አንድ አራተኞቹ ህፃናተ ነበሩ፡፡ የኢጣሊያን ጉዳይ ያየን እንደሆነ ደግሞ 72 በመቶዎቹ አብሯቸው የሚጓዝ አዋቂ ሰው የሌላቸው ናቸው”

ከተጎጂዎቹ መካከል የ 21 በመቶዎቹ ብቻ ነው እቅጩን ዕድሜያቸውን ማወቅ የተቻለው፤ ከነዚህ መካከል 58ቱ ከ 1 ዓመት እድሜ በታች የሆኑ ጨቅላ ህፃናት ሲሆኑ 67ቱ ደግሞ ከ 1 እስከ 5 ዓመት እድሜ ያላቸው ህፃናት ናቸው ለህልፈት የተዳረጉት፡፡

ለህፃናት ስደተኞቹ ሞት እንደ ዋነኛ ምክንያት ሆኖ የተጠቀሰው ባህር ላይ በመስጠም ለሞት መዳረግ ሲሆን፤ ከተመዘገቡት 681 ሟች ስደተኛ ህፃናት አብዛኞቹ የተከሰቱት የሜዲትራንያን ባህርን ወይም የቤንጋል የባህር ወሽመጥን ሲያቋርጡ ነው፡፡

የመኪና አደጋ፣ በመኪና በሚደረግ ጉዞ ውስጥ አየር አጥቶ መታፈን፣ ግጭት እና በሽታ በስደት ወቅት ለሚከሰት የህፃናት ሞት አውራ ምክንያቶች ናቸው፡፡

በቅርቡ፤ ከ 200 በላይ ስደተኞችን ከመጠን በላይ አጭቃ የጫነች የህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች መኪና በሊቢያዋ የባኒዋሊድ ከተማ አቅራቢያ በመገልበጧ ለአራት ህፃናት ሞት መንስኤ ሆኗል፡፡