የናይጄርያ ሴቶች ኢጣሊያ ውስጥ ከምንግዜም በከፋ መልኩ ወደ ሴተኛ አዳሪነት እንዲገቡ ይገደዳሉ

የፎቶ ምንጭ: ሬውተርስ

በሺዎች የሚቆጠሩ የናይጄርያ ስደተኛ ሴቶች እና ልጃገረዶች አውሮፓ ውስጥ ወደ ሴተኛ አዳሪነት እንዲገቡ በህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች የመገደድ አደጋ ተጋርጦባቸዋል ብሏል ዓለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት (ኣይኦኤም)።

ዓለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት ባወጣው መረጃ መሰረት፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት ወደ ኢጣሊያ ባህር አቋርጠው የሚደርሱ በአብዛኞቹ ታዳጊዎች የሆኑ ሴቶች ቁጥር ጨምሯል፤ ይህ ደግሞ በ 2006 ዓ.ም ከነበረው 1,454 ባለፈው ዓመት ወደ 11,000 ከፍ ብሏል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደገመተው በዚህ መልኩ ከሚደርሱት 80 በመቶ ያክሉ አብዛኛውን ግዜ በህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ሃሰተኛ “የነፃ ጉዞ” ቃል ተገብቶላቸው ከመጡ በኋላ ሴተኛ አዳሪ ሆነው እንዲሰሩ ይገደዳሉ።

“እነዚህ በየዓመቱ ዕድሜያቸው ለጋ እየሆነ የመጣው ልጃገረዶች ለፆታዊ ብዝበዛ ነው ወደ ኢጣሊያ እና አውሮፓ እንዲመጡ የሚደረገው” ብለዋል የዓለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት ቃል አቀባይ ፍላቪዮ ዲ ጂያኮሞ።

“በህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች  ይወሰዱና ከዚያ በኋላ ደግሞ በኢጣሊያ ጎዳናዎች ላይ ሴተኛ አዳሪዎች እንዲሆኑ ይገደዳሉ። አንዳንዴ ደግሞ፤ እኛ እስከምናውቀው ድረስ፤ እነዚህ ልጃገረዶች ስፔን፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ እና አውስትርያ ወደመሳሰሉት የአውሮፓ ሀገራትም ይላካሉ” ብለዋል ዲ ጂያኮሞ።

አብዛኞቹ ናይጄርያውያን ልጀገረዶች በኢዶ ግዛት ውስጥ ከሚገኙ ደሃ ቤተሰቦች የሚመጡ ናቸው። በኒጀር እና ሊቢያ አቋርጠው በሚመጡበት ረጅም ጉዞ ወቅት ከህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎቹ ጋር ግንኙነት ባላቸው ሴቶች ታጅበው ነው የሚጓጓዙት።

“እነዚህ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣው ታዳጊ ሴቶች ሴተኛ አዳሪነት ምን እንደሆነ፤ ወሲብ ምን ማለት እንደሆነ እንኳን የማያውቁ ናቸው”  ብለዋል ዲ ጂያኮሞ።