አፍሪካና የአውሮፓ ህብረት ስደተኞችን ከሊቢያ ወደሀገሮቻቸው ለመመለስ ተስማሙ
የፎቶ ምንጭ: ፍሊፕ ዎጃዘር/AFP/Getty Images. የአውሮፓና የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት ፎቶ ለመነሳት እንደቆሙ፡፡
የአፍሪካና የአውሮፓ ሀገራት ሊቢያ ውስጥ በሚገኙ የማጎርያ ማዕከላት ውስጥ ታስረው የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን አስወጥቶ ወደሀገሮቻቸው ለመመለስ የሚያስችል አስቸኳይ ዕቅድ ለመፈፀም ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡
የፈረንሳዩ መሪ ኢማኑዌል ማክሮን ይህን ተነሳሽነት ይፋ ያደረጉት አቢጃን ላይ በፈረንጆቹ ህዳር 29 የአውሮፓ ህብረት እና የአፍሪካ መሪዎች ባደረጉት ሌሎች ጉዳዮችንም የሚመክር ከፍ ያለ ስብሰባ ከተጠናቀቀ በኋላ ነው፡፡
ማክሮን ይህን “አስቸኳይ ዘመቻ” በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን ሲናገሩ፤ ከሊቢያ ወደሀገራቸው መመለስ የሚፈልጉትን ስደተኞች ለማስወጣት በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናቶች “በተጨባጭ መሬት ላይ የሚከወን ወታደራዊ እና የፖሊስ ዘመቻ” ብለው የገለፁት እንቅስቃሴ እንደሚከናወን ገልፀዋል፡፡ ዕቅዱ በጀርመን፣ ኢጣሊያ፣ እና ስፔን እንዲሁም ደግሞ ቻድ፣ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ፣ ሊቢያ፣ ኒጀር እና ሞሮኮ በተጨማሪም በከፍተኛ የአውሮፓ ህብረት፣ የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ባለስልጣናት ውይይት ተደርጎበታል፡፡
ሊብያም “ኢሰብአዊ ድርጊቶች ሲከወኑ የታየባቸውን ካምፖች” ላይ ለመግባት እንደምትፈቅድ ማረጋገጧ ጨምረው ተናግረዋል፡፡
የጀርመኑ የዜና ድርጅት DPA እንደዘገበው፤ ሰዎችን ከማጎርያ ማዕከላት በመፍታት፣ ስደተኞች ከየት እንደመጡ በመለየት፣ የጉዞ ሰነዶችን በመስጠት እና የመመለሻ ወጪያቸውን በመክፈል ረገድ የአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚነቱነ በመውሰድ ስራውን ያከናውናሉ፡፡
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ኤጀንሲዎች፤ UNHCR እና IOM በበኩላቸው ሰዎችን ወደሀገሮቻቸው መውሰድ ላይ ሚና ይጫወታሉ፤ የአውሮፓ ሀገረት ደግሞ ስደተኞችን ለመመለስ አዲስ ገንዘባዊ ድጋፍ ይሰጣሉ፡፡ አንዳንድ ከቻድ እና ኒጀር የመጡ በነዚህ ሀገራት ካይ ቅጣት ሊደርስባቸው የሚችል ስደተኞች አውሮፓ እንዲኖሩ ይደረጋል፡፡
ሊቢያ ውስጥ ስደተኞች ለባርነት ንግድ እና ሌሎች ጥቃቶች መጋለጣቸውን የሚያትቱ ዘገባዎች በእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ከአንድ ዓመት ለሚልቅ ግዜ ሲሰራጩ የቆየ ቢሆንም፤ ሁኔታውን ለመግታት ያለመው ይህ መግለጫ የወጣው የአሜሪካው ቴሌቪዥን CNN ሊቢያ ውሰጥ ሰዎች $400 ሲሸጡ የሚያሳይ ቪድዮ ካሳየ በኋላ ነው፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደሚለው፤ ሊቢያ ውስት በተደጋጋሚ ጭካኔ ለተሞላበት አያያዝ፣ ድብደባ፣ ማሰቃየት እና አስገድዶ መድፈር የተጋለጡ “በህገወጥ መንገድ በማጎርያ ማዕከላት ታስረው የሚገኙ ከ 20,000 በላይ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች” አሉ፡፡
“የሊብያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ኃይል እነዚህን ጥቃቶች ለማምለጥ የሚሞክሩ ስደተኞችን ባህር ላይ እየያዘ ወደ ማጎርያ ማዕከላቱ ይመልሳቸዋል” በማለት የአውሮፓ ህብረት ለነዚህ መሰል እንቅስቃሴዎች ድጋፍ እየሰጠ ነው ሲል ጠቅሷል፡፡
የአውሮፓ ህብረትም “ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎችን እና የወንጀለኞች ቡድኖችን ለመበጣጠስ” እንዲሁም ደግሞ “በጉዞው ወቅት አና በተለይም በሊብያ የስደተኞችን ሂወት ለመታደግ እና ለመጠበቅ” ሲባል ከአፍሪካ ህብረት ጋር “ጥምር የጋራ ግብረ ኃይል” እንደሚያቋቁም አስታውቋል፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ