ስደተኞች በሊቢያ ኢሰብአዊ በሆነ ሁኔታ ታስረዋል: የተመድ ሰብአዊ መብቶች ሃላፊ
የፎቶ ምንጭ: UNHCR/ አይሰን ፎንቴን
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር፤ በፈረንጆቹ ህዳር 14 እንደገለፁት፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ሊብያ በሚገኙ መንግስታዊ ማዕከላት ውስጥ “አስከፊ” እና “ኢሰብአዊ” በሆነ ሁኔታ ይታጎራሉ በማለት ተናግረዋል፡፡
ዘይድ ራአድ አል ሁሴን ይህን ያሉት ትሪፖሊ በሚገኙ አራት መንግስታዊ የማጎርያ ማዕከላት ላይ የተባበሩት መንግስታት ክትትል በሚያደርግበት ወቅት ከታሳሪዎች ጋር ቃለምልልሶች መደረጋቸውን ተከትሎ ነው፡፡
“ክትትል የሚያደርጉት ሰራተኞች ባዩት ነገር ደንግጠዋል: በሺዎች የሚቆጠሩ የከሱና የተጎሳቆሉ ወንዶች፣ ሴቶችና ህፃናት አንዳቸው ባንዳቸው ላይ ተደራርበው፣ ሰብአዊ ክብራቸው ተገፎ መሰረታዊ አገልግሎቶች በሌለባቸው መጋዝኖች ላይ ታጉረው ይገኛሉ” ሲሉ የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛው ኮሚሽን ፅህፈትቤት ቃል አቀባይ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡
በማዕከሉ የሚገኙ ታሳሪዎች ብዙ ግዜ ምግብ ወይም መድሃኒት እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ እንደሚደበደቡ ወይም በኤሌክትሪክ ሽቦ እንደሚቀጠቀጡ ተናግረዋል፡፡ በሽንት እና ሰገራ ሽታ በጠነቡ እነዚህ መጋዘን-መሰል ህንፃዎች ውስጥ በትክክል አገልግሎት የሚሰጡ መፀዳጃ ቤቶች የሉም፡፡ አስገድዶ መድፈር እና ፆታዊ ጥቃት የተለመደ ነው ተብሏል፡፡
የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛው ኮሚሽን ፅህፈትቤት እንዳለው፤ እነዚህ እስረኞች የእስራቸው ህጋዊነትን በተመለከተ ጥያቄ ማንሳት አይችሉም የህግ ድጋፍ ማግኘትም አይችሉም፡፡ በአሁኑ ወቅት 20,000 የሚደርሱ ሰዎች በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡
የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛው ኮሚሽን ፅህፈትቤት የሊቢያ ባለስልጣናትን በስራቸው በሚያስተዳድሯቸው ማጎርያ ማዕከላት ላይ የሚፈፀመውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዲያስወግዱ ያሳሰበ ሲሆን፤ ሊቢያ የሚገኙ ስደተኞች እያሳለፉ ያለውን “ለማሰቡ የሚከብድ አስከፊ ሁኔታ” በተመለከተ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ እንዳያልፈው አለምአቀፍ ማህበረሰቡን ጠርቷል፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ