ህገወጥ አዘዋዋሪዎች ብዙ ስደተኞችን በሰሜናዊ የኒጀር በረሃ ብቻቸውን ጥለዋቸው ጠፉ

Image source: Joe Penney/Reuters

የአካባቢው ባለስልጣናት እንዳስታወቁት፤ በሰሜናዊ ኒጀር የሰሃራ በረሃ ላይ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ብቻቸውን ጥለዋቸው ስለሄዱ ቢያንስ 51 ስደተኞች እንደሞቱ ተገምቷል።

የኒጄር ሰሜናዊ ክልል የቢልማ አስተዳዳሪ ፋቶሚ ቦውዶ “ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎቹ በአውላላው በረሃ ላይ ካለ ምግብ እና ውሃ ብቻቸውን ጥለዋቸው ሄዱ” ብለዋል።

ከጋምቢያ፣ ናይጄርያ፣ ሴኔጋልና አይቮሪኮስት የመጡ ሃያ አራት ከአደጋው የተረፉ ሰዎች ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎቹ ጥለዋቸው ከጠፉ በኋላ በረሃው ላይ እየተንከራተቱ ተገኝተዋል። እነዚህ ሰዎች መጀመርያ ላይ በሶስት መኪኖች ተጭኖ ወደ ሊቢያ ጉዞ የጀመረው ቢያንስ የ 75 ሰዎች ቡድን አካል ነበሩ።

ከአደጋው የተረፉት 24 ሰዎች ወደ ሴጉዌዲን ተወስደው ነበር፤ ቢሆንም ግን ከመካከላቸው አንዱ እዚያው ሲደርስ ሞቷል። የማዕከላዊ ኒጀርን በረሃዎች ለምን ያህል ግዜ በእግራቸው እንደተጓዙ ማወቅ አልተቻለም። ባለስልጣናቱ የቀሪዎቹን 51 ስደተኞች አስከሬን አሁንም በመፈለግ ላይ ናቸው፤ ጥረቱ በአሸዋ ማዕበል መነሳት ምክንያት ተስተጓጉሎ የነበረ ቢሆንም።

ቦውዶ “በ 65 ኪሜ ሬድየስ ውስጥ ለመፈለግ በተደረገው ጥረት ሊገኝ የቻለው የናይጄርያዊ ተማሪ መታወቂያ ወረቀት የተገኘበት አንድ አስከሬን ብቻ ነው” ብለዋል።

ራቅ ካለቸው የኒጀር አጋዲዝ ከተማ አንስቶ እስከ ሊቢያ ድንበር ድረስ የሚደረገው የ 750 ኪሜ ጉዞ በዚያ በሚጠብሰው የሰሃራ በረሃ ውስጥ ሳያቋርጡ ቢያንስ ለሶስት ቀናት መጓዝን ይጠይቃል።

“በረሃው ውስጥ ሂወት ማዳን ከምንግዜም በላይ አጣዳፊ ጉዳይ እየሆነ ነው። ከዓመቱ መባቻ አንስቶ፤ በዚሁ መስመር የሚጓዙ ሰለባዎችን እንድንታደጋቸው ተደጋጋሚ ጥሪዎችን ተቀብለናል” ብለዋል የዓለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት የኒጀር ልዑክ ኃላፊ ጁሴፔ ሎፕሬቴ።

በሂወት ከተረፉት መካከል ብቸኛዋ ሴት የ 22 ዓመቷ ወጣት ናት። “በአውሮፓ የተሻለ የወደፊት ዕድል እንደሚኖራት ተስፋ በማድረግ ነበር በሚያዝያ ወር መጀመርያ ላይ ከናይጄርያ የወጣችው” ብለዋል ሎፕሬቴ።

ናይጄርያዊቷ ሴት “በረሃው ውስጥ 10 ቀናት ቆይተናል። ከአምስት ቀናት በኋላ፤ ሹፌሩ ጥሎን ሄደ። ንብረቶቻችንን እንዳለ ነው ይዞ የሄደው፤ ከሰዓታት በኋላ ተመልሶ መጥቶ እንደሚወስደን ነበር የነገረን፤ ነገር ግን ተመልሶ አልመጣም” ትላለች።

ከስደተኞቹ መካከል 44ቱ በሁለት ቀናት ውስጥ ሲሞቱ፤ የተረፉት ሰዎች መጓዝ መጀመር እና እርዳታ መፈለግ እንዳለባቸው ወሰኑ።

ግንቦት 2015 ላይ የኒጀር መንግስት የስደተኞችን ህገወጥ ዝውውር የሚከለክል ህግ ያፀደቀ ሲሆን፤ ይህን ህግ ተላልፈው የሚገኙ ሰዎችም እስከ 30 ዓመት የሚደርስ እስራትና እስከ $51,000 የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት ይጠብቃቸዋል።