የሚድትራንያን ሃገራት መሪዎች ከሊቢያ ጋር በተደረሰው ስምምነት ተወያዩ
TMP – 21/04/2017
ይህ በጣልያን አስተናጋጅነት የተካሄደው የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ከሊቢያ ጋር የተደረሰው ስምምነት ለመደገፍ ነው፡፡ በየካቲት ወር ከሊቢያ ጋር የተደረሰው ስምምነት በሰሜን አፍሪካ የሚገኙ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች በመቆጣጠር ህገወጥ ስደተኞች የሊቢያ የባህር ዳርቻን መነሻ በማድረግ ወደ ጣልያን የሚያደርጉት ጉዞ ለመግታት ነው፡፡
የጣልያንና የአውሮፓ ህብረት ባለስልጣናት በተባበሩት መንግስታት የሚደገፈውን የሊቢያ መንግስት የሊቢያን የባህር ዳርቻ በመቆጣጠር ህገወጥ አዘዋዋሪዎች በሚድትራንያን ባህር በኩል የሚያደርጉት ህገወጥ የሰው ዝውውር ለመግታት የሚያስችለው የኢኮኖሚና የማቴርያል ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውም ገልጸዋል፡፡
የሊቢያው ጠቅላይ ሚኒስትር ፋየዝ አልስራጅ የሊቢያን የባህር ክልል ለመጠበቅና ለመቆጣጠር 800 ሚልዩን ዩሮ ድጋፍ ጠይቀዋል፡፡ በተጨማሪም ለባህር ክልል አሰሳና ጥበቃ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ማለትም ራዳር፣ 20 ጀልባዎች አራት ሄሊኮፕተሮችና ተሸርካሪዎች እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
የጣልያን የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሚኒቲ የመጀመሪያዎች 90 የሊቢያ ባህረኞች ስልጠና ማጠናቀቃቸው ገልጸው ኢጣልያ በግንቦት ወር መጀመሪያ ለባህር ክልል ጥበቃ የሚያገለግሉ 10 መርከቦች መስጠት ይጠበቅባታል ብለዋል።
አሁን በጣም ወሳኝ የሆነ መዋእለ ንዋይ ማቅረብ ያስፈልጋል ያሉት ሚኒቲ “ወሳኝ የሆነ የጋራ ቁርጠኝነት አሳይተናል የጋራ ዓላማ ያለው የጋራ ፍላጎት አለን፤ ይህም ስደተኞችን ለመጉዳት ሳይሆን ችግሩን በአግባቡ ለመቆጣጠር ነው” ብለዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽነር “እንደ አጋጣሚ ሆኖ ወደ ጣልያን የሚጓዙ ስደተኞች ቁጥር ጨምሯል ካሉ በኃላ “በዚህ ጫና ውስጥ ያለችዉ ብቸኛ ሃገርም ጣልያን ናት” ብለዋል።
የስምምነቱ አንዱ አካል በሊቢያ የባህር ጠባቂዎች በቁጥጥር ስር የሚውሉ ስደተኞች በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሚመራ ካምፕ ውስጥ በሊቢያ ለማስፈር ነው፡፡ ለዚህም የአውሮፓ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡
የጣልያኑ የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር በሁላችንም ትብብር እና የረድኤት ድርጅቶች ድጋፍ የሚሰራ መጠልያ ካምፕ ይኖረናል፤ ሊቢያ ውስጥ በሚሰራው መጠልያ የሚሰፍሩ ስደተኞች ወደ አውሮፓ ጥገኝነት መጠየቅ እንደሚችሉም ገልጸዋል፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ