ጣልያንና የደቡብ ሊቢያ የጎሳመሪዎች ህገወጥ ስደትን ለመከላከል ስምምነት አደረጉ
ከ60በላይ የደቡባዊው ሊቢያ ሳሃራ ክልል የጎሳ መሪዎች በሊቢያና የሚድትራንያን የባህር ክልል የሚደረገው ህገወጥ ስደትን ለመከላከል የተስማሙ ሲሆን ለዚህም ልማትን ለማከናወን የሚያስችል ድጋፍ ከጣልያን መንግሥት እደሚያገኙ ተገልጧል፡፡
ስምምነቱ በጣልያን መንግሥት አነሳሽነት የተደረገ ሲሆን ሃገሪቱ ከሊቢያ በሚዲትራንያን ባህር የሚደረግ የስደተኞች ጉዞ ወደአውሮፓ ለመሸጋገር እንደ ዋና መተላለፊያ በመሆኗ ነው፡፡ ጣልያን በበኩልዋ እነዚህ የጎሳ መሪዎች 5,000 ኪሎ ሜትር በሚሸፍነው የሳሃራ በረሃው ፌዛን ክልል ህገወጥ ስደትን ለመከላከል ሲተባበሩ ለመሰረተ ልማት ግንባታ፤ የገቢ ምንጭ የሚያገኙበት ስራ ለመፍጠርና፤ ለትምህርት ዕድል የሚውል ድጋፍ ታደርጋለች፡፡
ይህ በሮም ከተማ በጣልያን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሚኒቲ አደራዳሪነት በ60 ተፋላሚ የጎሳ መሪዎችን በአንድ መድረክ በማስማማት የተካሄደ ነው፡፡
የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሚኒቲ በወቅቱ “ደቡባዊው የሊቢያ ክልል በመጠበቅ ህገወጥ ስደትን መከላከል ማለት ደቡባዊውን የአውሮፓ ክልል እንደመጠበቅ ነው” ብለዋል፡፡ የቱዋሬግ፤ ቴቡ እና አውላድ ሱሌይማን ጎሳ መሪዎች ከጣልያን መንግሥት ድጋፍ ከተደረገላቸው 5,000 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የምዕራብ አፍሪካ ህገወጥ ስደተኞች መተላለፊያ የሆነው ኒጀር ድረስ ያለው ደቡባዊው ድንበር እንደሚዘጉት በሙሉ እምነት ተናግረዋል፡፡
የጎሳ መሪዎቹ በ2011 የሙዓመር ጋዳፊ መንግሥት መውደቅን ተከትሎ ከህገወጥ የሰው ንግድ ተጠቃሚ እንደነበሩ አምነው መሐመድ ሐይ ሳንዱ የተባሉ የቴቡ ጎሳ መሪ “የሙዐመር ጋዳፊ መንግሥት ከወደቀ በኋላ ድንበሩን የሚቆጣጠር አካል አልነበረም” ብለዋል፡፡ “ለአብዛኛዎቻችን ህገወጥ ስደተኞችን ማስተላለፍና ማስተባበር የገንዘብ ማግኛ ምንጫችን እየሆነ መጥቷል፤ ኢኮኖሚው እየተዳከመ በመምጣቱ የህዝባችን 15% ዋነኛ የገቢ ምንጭ በሆነው ህገወጥ የሰው ዝውውር ንግድ ስራ ተሰማርቷል” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
“ብዙዎቹ ወጣቶቻችን በስራ አጥነት ምክንያት ተስፋ ስለቆረጡ በድብቅ ህገወጥ የሰው ዝውውር ያከናውናሉ፡ ነገር ግን አስፈላጊ ስራ ከሰጠሃቸው ይህን ያቆማሉ ድጋፍና ልማት ከተደረገልን ይህን ንግድ በጋራ ለማቆም ዝግጁ ነን፤ ማንም ይህን ድንበር ማቋረጥ አይችልም፡” ሲሉም ሳንዱ በእርግጠኝነት ተናግረዋል፡፡
ጆፍ ፖርተር የተባሉ የሰሜን አፍሪካ የአደጋ መንስኤ አማካሪ የጎሳ መሪዎቹ እገዛ ውጤታማ እንደሚሆን በማመን “ጎሳዎቹ ድንበሩን ለሞቆጣጠርና የህገወጥ ስደተኞች ፍሰት ለመከላከል ብቃቱ አላቸው” ብለዋል፡፡
“5,000 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ድንበሩ ረጅም ቢሆንም ይህን ለማቋረጥ የሚያስቸግሩ በጣም ሰፋፊ ገላጣ መሬትና ተራሮችን ለማለፍ አይቻልም፥” ብለዋል፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ