ጣልያንና ጀርመን ሀገወጥ ስደተኞችን ለመከላከልና ለማስወጣት የሚያስችል እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀታቸው ኣስታወቁ

በኣዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፓውሎ ጀንቲሎኒ የሚመራው የጣልያን መንግስት ህገወጥ ስደተኞችን ለመከላከልና ለማስወጣት

የሚያስችል እርምጃ ለመተግበር የወሰነው ጣልያን ባለፈው 2016 የፈረንጆች አመት 180 ሺ ህገወጥ ስደተኞች ድንበርዋን

ጥሰው መግባታቸውን ተከትሎ ነው። ይህ ቁጥርም በጣም ከፍተኛና ሃገሪቱ ከዚህ በፊት ኣጋጥሟት የማያውቅ ክስተት በመሆኑ

ነው ሁለቱም መንግስታት ህገወጥ ስደተኞችን ለመከላከል የሚያስችል ኣዲስ ስትራተጂ ለመተግበር የተዘጋጁት።

አዲሱ የጣልያን የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ባለፈው ሳምንት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እውቅና አግኝቶ ድጋፍ ከተቸረው

የሊቢያ አንድነት መንግስት መሪ ፋይዝ አልስራጅ ጋር በትሪፖሊ ከሃገሪቱ እየተነሱ ወደ ጣልያን የሚገቡ ህገወጥ ስደተኞችን

ለመግታት የሚያስችል ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወቃል። በዋናነት ይህን ተግባር ለማከናወንም ጣልያን በሊቢያ ትሪፖሊ

ዘግታው የነበረው ኤምባሲዋን መክፈትዋ አይዘነጋም።

ይህ ጣልያን ከጊዚያዊው የሊቢያ መንግስት ያደረገችው ስምምነት የቀድሞው የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ሲልቪዮ በርሉስኮኒ

ከሞዓመር ጋዳፊ ጋር ፈጥረውት ከነበረው ወዳጅነት ለየት ያለ ስትራተጂካዊ ግንኙነት እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን የጣልያን የጦር

መርከቦች በሊቢያ የባህር ክልል ኣሰሳ በማካሄድ በህገወጥ ደላሎች ስደተኞችን ጭነው የሚጓዙ ጀልባዎችን ለመቆጣጠርና

ለመግታት እንዲሁም ወደ ሊቢያ ለመመለስ የሚያስችላቸው ስምምነት ነው ተብሏል። በተጨማሪም የበርካታ ህገወጥ ስደተኞች

መነሻ የተባለውን ደቡባዊው የሊቢያ የባህር ዳርቻ ለመቆጣጠር የሚያስችል ነው። ይህ የጣሊያን መንግስት አዲስ ስትራተጂ በሃገሪቱ

ውስጥ ጥገኝነት የጠየቁ ህገወጥ ስደተኞችም ጭምር ለማስወጣት ነው ተብሏል።

የጣሊያኑ የኣገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ሊቢያ ትሪፖሊ ከማምራታቸው በፊት በቱኒዝ ወደ ጣልያን በህገወጥ መንገድ የገቡትን

የቱኒዝያ ስደተኞች ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ከቱኒዝያ ባለስልጣናት ጋር መወያየታቸውም ተዘግቧል።

በታህሳስ 2016 አኒስ አምሪ የተባለ ቱኒዝያዊ የበርሊኑን የሽብር ጥቃት ከፈጸመ ከአንድ ሳምንት በኋላ በጣልያን ሚላን ውስጥ

የተገደለ ሲሆን የጣልያን መንግስትም በሃገሩ የሚገኙ ህገወጥ ስደተኞች ለማስወጣት የሚያስችሉ ማእከላት በሁሉም የጣልያን

ግዛቶች ለመክፈት እቅድ ለማውጣት እንደተገደደም የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትሩ አስታውቀዋል።

በተጨማሪም የጀርመን መንግስት በህገወጥ መንገድ ወደሃገሪቱ ገብተው የጥገኝነት ፍቃድ ያላገኙትን ስደተኞች ከመጠልያ

ጣብያቸው ለመመለስ የሚያስችል እቅድ ከመጪው መጋቢት ወር ጀምሮ ለመተግበር መዘጋጀቱ ኣስታወቀ። የጀርመን የሃገር

ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር እንዳስታወቀው ባለፈው ታህሳስ ወር ሃገሪቱ ያጋጠማትን የሽብር ጥቃት ተከትሎ ህገወጥ ስደተኞች

የማስወጣት ተግባር ኣጠናክሮ እንደሚቀጥልበት ገልጿል። ጀርመን ባለፈው 2016 የፈረንጆች ዓመት 25000 ተቀባይነት ያላገኙ

ህገወጥ ስደተኞች ያስወጣች ሲሆን 55,000 ደግሞ በገዛ ፈቃዳቸው ወደ ሃገራቸው እንደተመለሱ ተገልጿል።

ሁለቱም ሀገራት ህገወጥ ስደተኞችን ለመከላከልና ለማስወጣት ውሳኔ ላይ መድረሳቸው በሌሎች የአውሮፓ ህብረት አገራትና

እንዲሁም ባጠቃላይ በህብረቱ ውስጥ ህገወጥ ስደትን ለመከላከል የሚያስችል የጋራ ኣቋም እንዲኖር ተጽእኖ የሚፈጥር ነው

ተብሏል።