አብዛኛዎቹ አፍሪካዉያን ስደተኞች ሊያጋጥማቸው ስለሚችል አደጋ በቂ እውቀት ሳይኖራቸው ነው የሚሰደዱት

በ2016 መገባደጃ በአንድ ስደትን የሚከታተል የጥናት ተቋም የተሰበሰበ መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ 85%

ከምዕራብና ምስራቅ አፍሪካ የሚነሱ ስደተኞች በጉዞአቸው ወቅት ስለሚያጋጥማቸው አደጋ በቂ እውቀት ሳይኖራቸው ነው

የሚሰደዱት፡፡

የሰሜን አፍሪካ የስደት ጥናት ማዕከል (North Africa Mixed Migration Hub) ተብሎ የሚጠራው ተቋም

ከመጋቢት እስከ ታህሳስ 2016 ባሉት ወራት በ10 የጣልያን ከተሞች ከ341 ስደተኞች ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ

ስደተኞቹ ያለምንም መረጃ ወይም አነስተኛ እውቀት ነው ለስደት የሚነሱት፡፡ ከምዕራብ አፍሪካ የሚመጡ ስደተኞች

አነስተኛ እውቀት ያላቸው ሲሆኑ፤ ከሶማሊያ ፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ ከመሳሰሉ የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች የሚሰደዱ ሴቶች

በጉዞ ወቅት ስለሚያጋጥማቸው አደጋና መሰናክል በቂ ግንዛቤ ሳይኖራቸው እንደሚሰደዱ ጥናቱ ያመለክታል፡፡

ቃለ መጠይቅ ከሰጡት ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የጉዞውን አደጋ ከተመለከቱ በኋላ በውሳኔያቸው እንደሚፀፀቱ ሲገልፁ

45% ስለጉዞው በቂ እውቀት ቢኖራቸው ኖሮ በጭራሽ ለስደት እንደማይነሱ ተናግረዋል፡፡ በሌላ አማራጭ መስመር ይጓዙ

እንደነበር የገለፁት ደግሞ 12% ናቸው፡፡ ናይጄሪያና ኤርትራ ይህን አስቸጋሪና አደገኛ ጉዞ የሚመርጡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው

ስደተኞች የሚነሱባቸው ሀገሮች ሆነው ተመዝግበዋል፡፡

ሪፖርቱ ጨምሮ በህገወጥ ስደት ጉዞ ከሚያጋጥሙ አደጋዎች 78% በሊቢያ የሚደረገው ጉዞ እንደሆነና በሰሜን አፍሪካ

የሚደረገው የስደት ጉዞ ቀጣዩን ደረጃ ይዟል፡፡ በሊቢያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው በደል በስደተኞች ላይ እንደሚፈፀምም

ተገልጿል፡፡ 95% የሚሆኑት ስደተኞች ለአስገዳጅ ስራና ለጉልበት ብዝበዛ፥ 88% ያለምክንያት ለእስር እንደሚዳረጉ፥ 76%

ፆታዊ ጥቃት ሲፈፀም እንዳዩና እንዳጋጠማቸው ተናግረዋል፡፡ እንደ ሪፖርቱ ከሆነ ከሚፈፀሙት ፆታዊ ጥቃቶች 25%

በህገወጥ አዘዋዋሪዎች በሳሃራ ምድረ በዳ የሚፈፀሙ ናቸው፡፡ በተጨማሪም አዘዋዋሪዎቹ ለሹፌሮች እንደተጨማሪ

ክፍያ ሴት ልጆችን ለፆታዊ ጥቃት አሳልፈው እንደሚሰጥዋቸው ተናግረዋል፡፡ በጉዞ ወቅት ከሚፈፀሙ ፆታዊ ጥቃቶች

25% በአማፂዎች፣ ሽፍቶች፣ የምድረ በዳ ጎሳዎች፣ ሚሊሻዎች ወታደሮችና ፖሊሶች የሚፈፀሙ ናቸው፡፡

ሪፖርቱ ሲጠቃለል አደጋው በቂ ግንዛቤ ሳይኖራቸው በሚሰደዱ ስደተኞች ላይ የከፋ እንደሆነ ነው፡፡ ከአፍሪካ ከሚመጡ

ስደተኞች 14% የቀለም ወይም የሙያ ዲግሪ ሲኖራቸው አብዛኛዎቹ ግን መደበኛ ትምህርት ያልተማሩ ናቸው፡፡