የአውሮፓ ህብረት ለሊቢያ የሚደረግ የጀልባ ሽያጭ ክልከላን አፀደቀ
ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች በሜዲትራንያን በኩል ከሊቢያ ወደ ኢጣሊያ ሰው የማዘዋወር ተግባራቸውን በቀላሉ መከወን እንዳይችሉ ለማድረግ ሲባል፤ የአውሮፓ ህብረት ለአባል ሀገራቱ ወደ ሊቢያ የሚልኳቸው በአየር የሚሞሉ ጀልባዎችና ተገጣሚ ሞተሮች የውጪ ሽያጭ ላይ ገደብ እንዲያደርጉ ፈቃድ ሰጥቷል።
የመነሻ ሃሳቡ በሰኔ ወር መጀመርያ በማልታ የቀረበ ሲሆን፤ በሓምሌ ወር ደግሞ ከሊቢያ ወደ ኢጣሊያ የሚደረግ የስደተኞች ፍሰትን ለመቀነስ ያግዛል በሚል በ 28ቱ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ፀድቋል።
አሁን የአውሮፓ ህብረት ሀገራት፤ ጀልባዎችና ተያያዥ ዕቃዎች ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ሊጠቀሙባቸው ይችላሉ ብለው ለማመን በቂ ምክንያት በሚያገኙበት ወቅት፤ ለሊቢያ የሚደረግ የጀልባዎችና ተያያዥ ዕቃዎች የውጪ ንግድና አቅርቦትን መከልከል ይችላሉ። ክልከላው በአውሮፓ ህብረት በኩል የሚደረጉ የጀልባ ማስተላልፍ ስራዎችንም ያጠቃልላል።
በደንቡ መሰረት፤ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ሰዎችን ከሊቢያ ወደ ኢጣሊያ ለማሸጋገር ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ መሳርያዎችን ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ ላይ የተሰማሩ ላኪዎች አሁን ከመንግስታቸው ቀደም ብሎ የሚሰጥ ፈቃድ ያስፈልጋቸዋል።
“ከዛሬ ጀምሮ ወደ ሊቢያ የሚደረጉ በአየር የሚሞሉ ጀልባዎችና ሞተሮች የውጪ ንግድና አቅርቦት ላይ ገደቦችን ለማድረግ ውሳኔ ላይ ደርሰናል” ብለዋል የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሃላፊ ፈደሪካ ሞገሀሪኒ።
“እነዚህ መሳርያዎች በህገወጥ የሰው አዘዋዋሪች ለህገወጥ የዝውውር ተግባራት የሚውሉ ናቸው። ይህ በአውሮፓ ህብረት ደረጃ ያደረግነው ውሳኔ የህገወጥ አዘዋዋሪዎቹን ስራና ሂወት ይበልጥ ከባድ ለማድረግ የሚያግዝ ነው” ብለዋል ሞገሀሪኒ።
የአውሮፓ ህብረቱ መግለጫ እንደሚለው፤ ዕቃዎቹ ለአሳ አጥማጆች አገልግሎት እንዲሁም ሌሎች ጀልባዎችን ወይም ለጀልባዎቻቸው ሞተር የሚያስፈልጋቸው ትክክለኛ ተጠቃሚዎች አገልግሎት የሚውሉ ከሆነ ክልከላው የነዚህን ዕቃዎች የውጪ ንግድ የሚገድብ አይሆንም።
ፅሑፉን ያካፍሉ