ከ 34,000 በላይ ስደተኛ ህፃናት በኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ይመዘገባሉ
የኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተመላሻች ጉዳይ አስተዳደር (ARRA) በሚቀጥለው የትምህርት ዘመን ከ 34,000 በላይ ስደተኛ ህፃናት ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለማስተማር ዕቅድ መያዙን አስታውቋል፡፡
ከ ARRA የወጣ መግለጫ እንደሚያመለክተው፤ በ 27 የስደተኞች ካምፖች ውስጥ በአጠቃላይ 300 የመማርያ ክፍሎች እየተገነቡ ሲሆን የትምህርት መሳርያዎችም እየተሰጡ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ስደተኛ ተማሪዎች አጠቃላይ ቁጥር አሁን ካለበት 116,500 በሚቀጥለው የትምህርት ዘመን ወደ 151,000 ተማሪዎች ከፍ ለማድረግ የኢትዮጵያ መንግስት ዕቅድ አለው ብሏል ARRA፡፡ የስደተኞች ጉዳይ ባለስልጣኑ በሚቀጥለው የትምህርት ዘመን በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ስደተኛ ተማሪዎች ቁጥር ወደ 2,500 በላይ ከፍ ለማድረግም እየሰራ ነው፡፡
በተጨማሪም፤ የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ ውስጥ ለሚኖሩ ስደተኞች የልደት፣ ጋብቻ፣ ፍቺና ሞትን ጨምሮ፤ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎት እንደሚጀምርም አስታውቋል፡፡
ቀደም ሲል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ስደተኞች እንዲህ የመሳሰሉትን የወሳኝ ኩነቶች ህጋዊ ምዝገባ ለማግኘት ይቸገሩ ነበር፡፡ ይህ ማለት ደግሞ፤ ከልደት እና ጋብቻ ምዝገባ ጋር ተያያዠ የሆኑ ሰነዶችን ለማግኘት ሲሉ ሱዳን እና ዩጋንዳ ወደመሳሰሉት ሀገራት በህገወጥ መንገድ ለመሰደድ ግድ ይላቸው ነበር፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ከ 800,000 በላይ ስደተኞችን ተቀብላ እያስተናገደች ሲሆን፤ ከነዚህም አብዛኞቹ ከኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን የመጡ ናቸው፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ