አራተኛ የነፍስ አድን ቡድን በሜዲትራንያን የሚያከናውነውን ስራ አቆመ

ሜዲትራንያን ባህር ላይ የአሰሳና የነፍስ አድን ስራ የሚያከናውን አራተኛ ድርጅት የደህንነት ስጋት እና “እየጨመረ የመጣውን አለመረጋጋት” በመጥቀስ ስደተኞች የመታደግ ስራውን እንደሚያቆም አስታውቋል፡፡
መቀመጫውን በማልታ ያደረገውና በፈረንጆቹ 2014 የተመሰረተው Migrant Offshore Aid Station (MOAS) የተሰኘው የባህር ዳርቻ አቅራቢያ የዕርዳታ ጣቢያ እስከ 40,000 የሚደርሱ ስደተኞችን ሂወት ከሜዲትራንያን ባህር ታድጓል፡፡
ሜዲትራንያን ላይ በግል የገንዘብ ድጋፍ የነፍስ አድን ስራ የሚያከናውን የመጀመርያውን መርከብ የሚያንቀሳቅሰው MOAS፤ ከሊቢያ ወደ ኢጣሊያ በሜዲትራንያን የሚሻገሩ ስደተኞችን የመታደግ ስራውን ያቆመ አራተኛው ድርጅት ነው፡፡
ባለፈው ወር፤ Medecins sans Frontieres በመባል የሚጠራው ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን፣ በመቀጠልም ሴቭ ዘ ችልድረን እና የጀርመኑ ሲ አይ የተሰኙት ድርጅቶች ስራዎቻቸውን አቁመዋል፡፡ የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ኃይል ከሚያሳየው ሞገደኝነት የተነሳ ሰራተኞቻቸው ከእንግዲህ በኋላ ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ ስራዎቻቸውን ማከናወን እንዳልቻሉ ነው የገለፁት፡፡
MOAS በፈረንጆቹ መስከረም 4 ሜዲትራንያን ላይ ስደተኞችን የመታደግ ተግባራቱን ለማቆም ለምን እንደወሰነ ሲገልፅ፤  “ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረ የመጣ ውስብስብ ሁኔታ” ምክንያት መሆኑን አስፍሯል፡፡ በምትኩ ፎኔክስ የተሰኘችውን መርከቡን በማያንማር የተከሰተውን ግጭት ሸሽተው ወደ ባንግላዲሽ በመሄድ ላይ የሚገኙትን የሮሂንጊያ ስደተኞችን ለመርዳት ወደ ቤንጋል የባህር ወሽመጥ ሊልክ ነው፡፡
“ከአሁን በኋላ ደህንነቱ ወደተጠበቀ ወደብ ይወሰዱ እንደሆን እርግጥ የሆነ መረጃ የለንም፤ ተመልሰው ወደ ሊቢያ ተገደው የሚላኩ ስደተኞችን በመታደግ የሃሰት ተስፋ መስጠት አንፈልግም፡፡” ብለዋል ከባለቤታቸው ጋር በመሆን MOAS ን የመሰረቱት ወይዘሮ ረጂና ካትራምቦን፡፡
“እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ማንም ቢሆን ትኩረት በማይችርበት ሁኔታ ላይ MOAS ተሳታፊ የመሆን ፍላጎት የለውም፤ ከዚህ ይልቅ ከባህሩ ወዲያ ታግተው በሚቆዩበት ጊዜ ለሚኖራቸው ዕጣፈንታ ግድ ባለመስጠት ትኩረት እየተደረገ ያለው ወደ አውሮፓ የባህር ዳርቻዎች እንዳይደርሱ መከላከል ላይ ብቻ ነው” ብለዋል ካትራምቦን፡፡
በቅርቡ፤ የስደተኞችን ፍሰት ለመቀነስ ከኢጣሊያ የባህር ኃይል የስልጠና እና የቁሳቁስ ድጋፍ የተሰጠው የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ኃይል በዕርዳታ ሰጪ ቡድኖች ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጠንከር ያሉ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው፡፡
ዕርዳታ ሰጪዎች ባህር ላይ ይታደጓቸዋል በሚል እሳቤ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ደካማ እና ከመጠን በላይ የታጨቁ ጀልባዎች ላይ ስደተኞችን ጭነው እንዲልኩ እያበረታቱ ነው ሲሉ የኢጣሊያና የሊቢያ ባለስልጣናት የእርዳታ ድርጅቶችን ይወቅሷቸዋል፡፡