በቱኒዝያ አቅራቢያ የስደተኞች ጀልባ ከጦር መርከብ ጋር በመላተሟ ብዙ ስደተኞች ሞቱ
የፎቶ ምንጭ፡ AFP
ስደተኞች የተሳፈሩባት ጀልባ ከጦር መርከብ ጋር በተላተመች በሳምንቱ የቱኒዝያ የባህር ኃይል የ 26 ስደተኞችን ሬሳ በባህር ላይ ማግኘቱን የቱኒዝያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል፤ ይህም የሟቾችን ቁጥር 34 አድርሶታል፡፡
ግጭቱ ያጋጠመው በፈረንጆቹ ጥቅምት 8 ሲሆን ከቱኒዝያ የባህር ጠረፍ 54 ኪሎሜትር ራቅ ብሎ የቱኒዝያ የባህር ኃይል መርከብ 80 የሚደርሱ ወደ አውሮፓ ሲጓዙ የነበሩ ስደተኞችን ከጫነች የእንጨት ጀልባ ጋር በመላተሟ ነው፡፡
የባህር ኃይሉ መርከብ በጀልባዋ ላይ የተሳፈሩትን ሰዎች ማንነት ለማወቅ ወደ ጀልባዋ በተጠጋች ግዜ ነው ግጭቱ ያጋጠመው ተብሏል፡፡
የማልታ ባለስልጣናት ከኢጣሊያ እና ቱኒዝያ የባህር ኃይል ጋር ተቀናጅተው ባስተባበሩት የነፍስ አድን ዘመቻ የ 38 ስደተኞችን ሂወት መታደግ የቻሉ ሲሆን በወቅቱ 8 ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል፡፡
ግጭቱ ካጋጠመ ከአንድ ሳምንት በኋላ የቱኒዝያ የነፍስ አድን እና አሰሳ መርከብ ሰራተኞች የጀልባዋን ቅሪት በማየት ተጨማሪ 26 ሬሳዎችን በሁለት ቀናት ውስጥ ከባህሩ ላይ ማንሳት ችለዋል፡፡
ከአደጋው በኋላ የነፍስ አድን ሰራተኞች የታደጉት አንድ ስደተኛ ጀልባዋ ላይ 90 ሰዎች ተሳፍረው ነበር ሲል ለ AFP ተናግሯል፤ ይህም ማለት ደግሞ እስከ 24 የሚደርሱ ስደተኞች በባህሩ ሞተዋል አሊያም የደረሱበት አልታወቀም ተብሎ ይገመታል፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ