ከሚያዝያ ወር ጀምሮ 1,000 የሚሆኑ ሰደተኞችን በኒጀር በረሃ መታደግ ተችሏል

አይኦኤም ከኒጀር የሲቪል ጥበቃ ጓድ ጋር በአንድነት፡፡ ፎቶ፡ የተባበሩት መንግስታት የስደት ጉዳዮች ኤጀንሲ (አይኦኤም) 2017

ዓለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ነሓሴ 3 ላይ እንዳስታወቀው፤ የስደተኞች ፍለጋና ሂወት አድን ዘመቻው ከሚያዝያ ወር ጀምሮ በኒጀር ሰሜናዊ በረሃ ላይ የ 1,000 ስደተኞችን ሂወት መታደግ ችሏል፡፡
ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ስደተኞችን በኒጀር ሰሜናዊ ክፍል በተደጋጋሚ ብቻቸውን ጥለዋቸው ይጠፋሉ፤ ይህ አካባቢ ስደተኞች እጅግ ደካማ በሆኑ ጀልባዎች ተጭነው አውሮፓ ለመድረስ በማቀድ መንገድ ወደሚጀምሩባት ሊቢያ የመሻገርያ ቀጠና ነው፡፡
ቀደም ሲል ቀንደኛ የሰዎች ዝውውር ማዕከል ከነበረችው የኒጀርዋ አጋዴዝ ከተማ ተነስተው መንገድ የሚጀምሩ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ቁጥር በቅርቡ እየቀነሰ ሲሆን፤ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎቹ እንዳይያዙ በመስጋት በአሁኑ ሰዓት በሰሃራ በረሃ በኩል የማይታወቁ መንገዶችን እየተጠቀሙ ይገኛሉ፡፡
“አዘዋዋሪዎቹ ከዋና ዋና ማእከላት፣ ኬላዎችና የህግ ቁጥጥር ለመራቅ ሲሉ የበለጠ አደገኛ መንገዶችን እየተጠቀሙ ነው” ብለዋል በኒጀር የዓለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት መርሃግብር ስራ አስኪያጅ የሆኑት አልቤርቶ ፕሬቶ፡፡
“ነገር ግን መኪኖቸ ይሰበራሉ፣ ሹፌሮች ይጠፋሉ እንዲሁም ደግሞ ስደተኞች ብቻቸውን ይተዋሉ … ሁኔታዎቹ አስከፊ ናቸው፡፡ ስደተኞች ‘በረሃው ከሜዲትራንያን የሰፋ የመቃብር ቦታ ነው’ ነው የሚሉት”  ሲሉ አክለዋል ፕሬቶ፡፡
ባለፈው የሓምሌ ወር የመጨረሻ ሳምንት፤ አይኦኤም ከኒጀር የሲቪል ጥበቃ ክፍል ጋር በመተባበር በኒጀር ሰሜናዊ በረሃ እንዲሁም ከ 1,400 ኪሎሜትሮች በላይ በሚሸፍነው ከሊቢያ ጋር በሚዋሰነው ድንበር አካባቢ የሚገኙ የህገወጥ ስደት መስመሮችን ለመለየት ዳሰሳ አድርጎ ነበር፡፡
“በቶውሞ ከሚገኘው የኒጀርና ሊቢያ ድንበር ብዙም ሳይርቅ፤ በአብዛኛው ከናይጄርያ እና ጋና የመጡ ሴቶች የሚገኙበት አንድ ትልቅ የስደተኞች ስብስብ ከድንበር ኬላው አጠገብ አንድ ጭለማ መጋዘን ውስጥ ተኝተው ወደ ሰሜን አቅጣጫ የሚያደርጉትን ቀጣይ ጉዞ እየተጠባበቁ ስናገኛቸው በጣም ነበር የደነገጥኩት” ብለዋል ፕሬቶ፡፡
በአሁኑ ሰዓት በሰሃራ በረሃ የሚሞቱ ስደተኞች ቁጥር የሚገልፅ መረጃ የለም፡፡
“ምክንያቱም በረሃው እጅግ ሰፊ ነው … በዚህ መንገድ ላይ በእርግጥ ስንት ሰዎች እየሞቱ እንደሆነ ማወቅ ከባድ ነው” ብለዋል የአይኦኤም ቃል አቀባይ ኦሊቭያ ሄደን፡፡ “ነገር ግን በመቶዎች ወይም በሺዎች የሚቆጠር እንደሆነ እርግጥ ነው” ሲሉ ጨምረዋል፡፡
በቅርቡ በኒጀር ከተደረጉት የአይኦኤም የስደኞች ፍለጋና ሂወት አድን ዘመቻዎች በአንዱ፤ ሹፌሮቻቸው ጥለዋቸው የጠፉ አንዲት የ 7-ዓመት-ልጅ የምትገኝባቸው 23 የጋምቢያ እና ሴኔጋል ስደተኞችን መታደግ ተችሏል፡፡
“ህገወጥ የሰው ዝውውር እና ሽግግር መረቦች እንዴት እንደሚገናኙ ይበልጥ መረዳት እንፈልጋለን፤ እንዲሁም ደግሞ ለስደተኞች መረጃ፣ ድጋፍ እና አማራጮችን ማቅረብ ያስችለን ዘንድ ራቅ ባሉት አካባቢዎች ላይ ይበልጥ መገኘት እንፈልጋለን” ብለዋል አልቤርቶ ፕሬቶ፡፡