በሊቢያ የሚገኙ እስር ቤቶችን ለማሻሻል ኢጣልያ ገንዘብ መደበች
ሊቢያ ውስጥ ባሉ እስር ቤቶች ታጉረው ለሚገኙ ስደተኞች የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን ለማሻሻል የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን (NGOዎች) ለመደገፍ ኢጣሊያ ስድስት ሚልዮን ዩሮ መድባለች፡፡
ሊቢያ ውስጥ በሚገኙ እስር ቤቶች ለመስራት ፍላጎቱ ላላቸው መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተሰናዳው ይህ የስድስት-ሚልዮን-ዩሮ ጨረታ “በቅርቡ፤ በዚህ ወር መጀመርያ ላይ” ይጀመራል ሲሉ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትሩ ማርዮ ጊሮ ለኢጣሊያ ሚዲያ ተናግረዋል፡፡
“የሊቢያ ባለስልጣናትም ሙሉ ለሙሉ ተሳታፊ ይሆናሉ፤ ፍቃድ እንዲሰጡን እየጠየቅን ነው” ብለዋል ጊሮ፡፡
ጊሮ ከእርሳቸው ጋር በሮም በተካሄደ ስብሰባ ላይ ተሳታፉ ለነበሩ በርካታ ሰብአዊ ዕርዳታ ሰጪ ቡድኖች እና ለጋሾች እንዲሁም ፍላጎቱ ያላቸው መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡ “እነዚህን ሰዎች ገሃነም ላይ ልንተዋቸው አንፈልግም” ብለዋል ጊሮ፡፡
“ለዚህም ነው የኢጣሊያ ዓለምአቀፍ የትብብር ኤጀንሲ… የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጀንሲንም ሆነ ዓለምአቀፉን የፍልሰተኞች ድርጅትን ሳይጠብቅ እርምጃ እየወሰደ ያለው” በማለት ጊሮ አብራርተዋል፡፡
የስደተኞች ማቆያ እስር ቤቶች ለሚገኙባቸው አነስተኛ የሊቢያ ከተሞችም ተጨማሪ ሶስት ሚልዮን ዩሮ ይመደባል፡፡
በሜዲትራንያን በኩል የሚደረገውን የስደተኞች ፍሰት በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ እየተደረገ ባለው ጥረት ውስጥ፤ ይህ መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍ በኢጣሊያ መንግስት እየተወሰዱ ካሉ ተከታታይ እርምጃዎች አዲሱ ነው፡፡ በተጨማሪም ኢጣሊያ በሜዲትራንያን ባህር ላይ በሊቢያና ኢጣሊያ መካከል ስደተኞችን የመታደግ ተግባር የሚያከናውኑ ድርጅቶች ተገዢ የሚሆኑበትን የስነምግባር ህግ ያወጣች ሲሆን በተጨማሪም የስደተኞችን ፍሰት ለመቀነስ ለሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ኃይል ድጋፍ እያደረገች ነው፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ