የሱዳን ፍርድቤቶች ኤርትራውያን ስደተኞችን ወደሀገራቸው መለሱ

የሱዳን ፍርድቤቶች በነሓሴ ወር በርካታ ኤርትራውያን ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው መልሰው የላኩ ሲሆን ሌሎችን ደግሞ ‘በህገወጥ መንገድ ወደ ሱዳን ግዛት ሰርጎ በመግባት’ ወንጀል የእስር ቅጣት አስተላልፈውባቸዋል፡፡
ባለፈው ወር፤  በበካርቱም እና ከሰላ  የሚገኙ ፍርድቤቶች 44 ሴቶች የሚገኙባቸውን 104 ኤርትራውያንን ወደ ሀገራቸው መልሰዋል፡፡ አርባ አራት ሰዎች ደግሞ ፍርዳቸውን እየተጠባበቁ በኦምዱርማን ቀርተዋል፡፡
ስደተኞቹ ከአንድ ወር በፊት ወደ ሊቢያ በሚያቀኑበት ወቅት፤ ፈጣን ድጋፍ ሰጪ ኃይል ተብለው በሚጠሩት የሱዳን መንግስት የሚሊሺያ ኃይሎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን በፈረንጆቹ ነሓሴ 24 ወደ ፍርድ ከመቅረባቸው በፊት ኦምዱርማን ውስጥ ታስረው ቆይተዋል፡፡
ነሐሴ 29፤ በከሰላ ከተማ የሚገኝ ፍርድ ቤት ሌሎች 30 ወጣት ኤርትራውያን ስደተኞች ወደሀገራቸው እንዲመለሱ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ሌሎች ስልሳ ስድስት ስደተኞች በህገወጥ መንገድ ወደ ሱዳን ግዛት ሰርጎ በመግባት ወንጀል የሁለት ወር እስራት የተፈረደባቸው ሲሆን መስከረም አጋማሽ ላይ የእስር ቅጣታቸውን አንደጨረሱ ወደሀገራቸው ተመልሰው ይላካሉ፡፡
በሓምሌ ወር መጀመርያ፤ በምስራቅ ሱዳን ዋድ አል ሂልዮ ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ላይ በተደረገ ዘመቻ  35 ሴቶች የሚገኙባቸው  ሌሎች 66 ኤርትራውያን ስደተኞች በቁጥጥር ስር ውለው ነበር፡፡ እስራታቸውን ተከትሎ፤ ስደተኞቹ ለስደተኞች ጉዳይ ፖሊስ ተላልፈው የተሰጡ ሲሆን ከሰላ ወደሚገኝ እስርቤትም ተልከዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ሓምሌ ወር ላይ፤ የሱዳን ሰሜናዊ ክልል አስተዳዳሪ አደገኛ ዕፅ እና ሰዎችን የሚያዘዋውሩ የወንጀለኞች ቡድኖች በክልሉ እያለፉ ነው የሚል ቅሬታ ካቀረቡ በኋላ ፈጣን ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች ራቅ ብሎ በሚገኘው የዚሁ ክልል በረሃ ላይ እንዲሰፍሩ ተደርጓል፡፡
ፈጣን ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች በያዝነው ዓመት መጀመርያ ላይ እንዳሉት፤ በፈረንጆቹ 2016 የመጨረሻ ሰባት ወራት በሱዳን-ሊቢያ ድንበር አካባቢ የ 1,500  ህገወጥ ስደተኞችን ዝውውር ማስቆም ችለዋል፡፡
በቅርቡ በሰጡት መግለጫ፤ ወደ ሊቢያ ሲያቀኑ የነበሩ አምስት ሴቶች የሚገኙባቸው 21 ህገወጥ ስደተኞች መመያዛቸውን  ፈጣን ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች በፈረንጆቹ መስከረም 14 ተናግረዋል፡፡
ሱዳን “የስደት ጉዳዮች አስተዳደር ሂደትን ለማሻሻል” እና “በሀገሪቱ ለህገወጥ ስደት የሚገፉ ዋና መንስዔዎችን ለመከላከል” የሚውል 155 ሚልዮን ዩሮ የአውሮፓ ኮሚሽን የልማት እርዳታ ተጠቃሚ ስትሆን፤ ይህም ለአፍሪካ የሚሰጠው የአውሮፓ ህብረት የኢመርጀንሲ ትረስት ፈንድ አንድ አካል ነው፡፡