ጀርመን የመጨረሻዎቹን ጥቂት ስደተኞች ከግሪክ እና ከጣሊያን ልትወስድ ነው

የፎቶ ምንጭ: dpa- የጀርመን ፕሬስ ድርጅት

የጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በፈረንጆቹ ጥር 29 እንዳስታወቀው፤ የአውሮፓ ህብረት ስደተኞችን ለማስፈር ያወጣው ዕቅድ የተገባደደ በመሆኑ፤ ጀርመን ከጣሊያን እና ግሪክ ጥቂት በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ብቻ ነው ወስዳ የምታሰፍረው፡፡

የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አነርት ኮርፍ ለዶቼቬሌ (DW) እንደተናገሩት፤ ሀገሪቷ እስካሁን ከሌሎች የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት በላቀ ብዙ ስደተኞችን ወስዳ አስፍራለች፡፡ ጀርመን የአውሮፓ ህብረት ስደተኞችን ለማስፈር ባወጣው አሰራር 27,000 ስደተኞችን ወስዳ እንድታሰፍር ቢመደብባትም 10,000 ብቻ ነው የተቀበለችው፡፡

ይህንን በተመለከተ ሲያብራሩ፤ ስደተኞች የዚህ መርሃግብር ተጠቃሚ ለመሆን አመልካቾቹ ጥገኝነት የማግኘት ዕድል ቢያንስ 75 በመቶ ከሆነባቸው ሀገራት የመጡ መሆን ይኖርባቸዋል፤ መጀመርያ ከተጠበቀው አንፃር እጅግ በጣም ጥቂት ሰዎች ናቸው መስፈርቱን ማሟላት የቻሉት ብለዋል ኮርፍ፡፡

“ስደተኞችን ወስዶ የማስፈር መርሃግብሩ በመስከረም ወር 2017 ላይ አብቅቷል፤ ይህ ማለት ከዛን ግዜ ጀምሮ የመጡ አመልካቾች የዕድሉ ተጠቃሚ አይሆኑም” ሲሉ ጨምረዋል አነርት ኮርፍ፡፡

“ጀርመን የቀሩባትን የማስፈር ስራዎች በ 2017 መጨረሻ ላይ አጠናቃለች፡፡ በሚቀጥሉት ሳምንታት፤ ጀርመን ካለፈው ዓመት የቀሩ አንዳንድ ያልተሟሉ የማስፈር ጉዳዮችን ብቻ ነው የምታስጨርሰው”
በፈረንጆቹ 2015 የስደተኞች ቀውስ መጀመርያ ላይ የተጀመረው የአውሮፓ ህብረት ስደተኞችን ወስዶ የማስፈር እቅድ መሰረት፤ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት 160,000 ያክል ጥገኝነት ጠያቂዎችን

እስካለፈው መስከረም ወር ድረስ ከኢጣሊያና ግሪክ ወስሰው ለማስፈር ተስማምተው ነበር፡፡ በኋላ ላይ የአውሮፓ ህብረት ባለስልጣናት የዕድሉ ተጠቃሚ መሆን የሚገባቸው ስደተኞች በቁጥር ከዚህ ያነሱ መሆናቸውን በመረዳት ይህ ቁጥር ወደ 100,000 ዝቅ እንዲል ተደርጓል፡፡