ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ለመመለስ የአውሮፓ ህብረት እና ኢትዮጵያ ሊተባበሩ ነው
የፎቶ ምንጭ: ኢዜአ / ሰኔ 2008 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የሁለትዮሽ ስምምነት ሲፈራረሙ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት፤ በአሁኑ ወቅት አውሮፓ ውስጥ በመኖር ላይ የሚገኙ ነገር ግን አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶች የሌላቸው ወይም ደግሞ ተቀባይነት ያለው የጥገኝነት ማመልከቻ የሌላቸውን ዜጎቹን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ተባብሮ እየሰራ ነው፡፡
“መጀመርያ ላይ አባል ሀገሮች የኢትዮጵያ መንግስት ስደቶቹን ለይቶ እንዲያውቅላቸው የስደተኞቹን ስም ለኢትዮጵያ ይሰጣሉ፤ ከዚያም ለጉዞ አስፈላጊ የሆኑትን ሰነዶች እናዘጋጃለን፤ በመቀጠልም ስደተኞችን የመመለስ ሂደት ተግባራዊ ይሆናል” ሲሉ በአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አቶ ቶሾመ ቶጋ ለ EU Observer ተናግረዋል፡፡
አምባሳደሩ እንዳብራሩት ከሆነ፤ በአውሮፓ የሚገኙና ፖለቲካዊ ጥገኝነት ወይም ደግሞ ህጋዊ የሞኖርያ ፈቃድ ያገኙ ኢትዮጵያውያን በዚህ አሰራር የሚደርስባቸው ምንም ተፅዕኖ አይኖርም፡፡ በተጨማሪም ሀገራቸው የምትቀበለው ወደሀገራቸው መመለስ የሚፈልጉ ዜጎችን ብቻ ነው ብለዋል፡፡
ዜጎቹ ከአውሮፓ ወደሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ፤ የአውሮፓ ህብረት የልማት ኮሚሽን ስደተኞቹ ከማህበረሰባቸው ጋር ለመቀላቀል የሚያስችላቸውን ወጪ ይሸፍናል፡፡
“የኢትዮጵያ መንግስት በዚሁ አሰራር የሚመለሱ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ከማህበረሰባቸው ጋር ለማቀላቀል በሚያደርጉት ጥረት የአውሮፓ ህብረት ተገቢ በሆኑ ፕሮጀክቶች አማካኝነት ድጋፍ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት ገልጧል” ሲል የስምምነቱ ረቂቅ ሰነድ ያስቀምጣል፡፡
በዚህ ሰነድ መሰረት፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የደህንነትና ፀጥታ አገልግሎት መስርያ ቤት፤ አስፈላጊ ሰነዶች የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ዜግነታቸውን በተመለከተ ውሳኔ በመስጠት ላይ ድጋፍ ለማድረግና እና አስፈላጊ የሆነውን የጉዞ ሰነድ በመስጠት ረገድ ድጋፍ ያደርጋል፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ