በማዕበል የተገፋ የ11 ስደተኞች ሬሳ ብትራብሉስ ባህር ዳርቻ መገኘቱ የሊብያ ቀይ ጨረቃ ማህበር ገለጸ

በህይወት ማዳን ሥራ የተሰማሩ የሊቢያ ቀይ ጨረቃ አባላት በማዕበል የተገፉ የ11 ስደተኞች ሬሳ በትራብሉስ የባህር ዳርቻ በፈረንጆች አቆጣጠር ታህሳስ 28/2016 መሰብሰባቸው ገለፁ፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች በማዕበል የተገፉ ሬሳዎች በማየት በሰጡት ጥቆማ መሰረት የማህበሩ የነብስ አድን ስራ አባላት በባህር ዳርቻው ተገኝተው ባካሄዱት አሰሳ በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በባህር ሊሻገሩ ሲሉ የሞቱ የ11ስደተኞች ሬሳ መሰብሰባቸው የረድኤት ድርጅቱ ቃል አቀባይ ተናግረዋል፡፡
የሊቢያ ቀይ ጨረቃ ማህበር በማህበራዊ ድረገፁ እንዳሰፈረው ከሆነ፡ የህገ ወጥ ስደተኞች ሬሳ ከሕያል- እንዳሉስ- ትራብልስ ከተማና ከከተማዋ በስተምዕራብ በኩል 11ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው አካባቢ የተሰባሰቡ ናቸው፡፡
በሊቢያ ከፈረንጆቹ 2011 ጀምሮ በተከሰተው የጎሳ ግጭት ሳቢያ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት ባለመመስረቱ ምክንያት የህገ ወጥ ስደተኞች አስተላላፊ ደላሎች ይህን ክፍተት እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው በርካታ ህገ ወጥ ስደተኞችን ወደ አዉሮፓ ለማሸጋገር ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ንግድ ላይ እንደተሰማሩ ነው የሚገለፀው፡፡
በዚህም መሰረት በመቶ ሺዎች የሚገመቱ ስደተኞች ዋስትና በሌለውና ከፕላስቲክና እንጨት በተሰሩ ትናንሽ ጀልባዎች ከመጠን በላይ ተጨናንቀውና ታጭቀው አደገኛ እና አስፈሪ የባህር ማዕበል ይከሰትበታል ተብሎ በሚነገርለት ማእከላዊ የባህር ክልልን አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመሻገር እንደሚደፍሩት ነው የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት ዘገባ የሚያስረዳው፡፡ ወቅታዊው የድርጅቱ ዘገባ እንደሚገልፀው ከሆነ በ2016 የፈረንጆች ዓመት ውስጥ ማዕከላዊውን የባህር ክልል አቋርጠው ወደ አውሮፓ ከገቡት 360/ ሶስት መቶ ስልሳ ሺህ / ህገ ወጥ ስደተኞች ውስጥ 180/አንድ መቶ ሰማኒያ ሺዎቹ/ ጣሊያን የገቡ ሲሆን 5000/አምስት ሺህ/ ስደተኞች ግን ህይወታቸው በባህር ውስጥ አጥተዋል ፡፡
በዚህም መሰረት ባለፈው 2016 የፈረንጆች ዓመት በማዕከላዊ የባህር ክልል የጠፋው የህገወጥ ስደተኞች ህይወት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከተመዘገበው ጋር ሲነፃፀር በ25 በመቶ መጨመሩን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት ባወጣው ወቅታዊ ዘገባ ገልፃል ፡፡