የአውሮፓ ህብረትና ቱርክ ስምምነት አንድ ዓመት በኋላ ህጻናት ስደተኞች እየተሰቃዩ ነው

TMP – 15/04/2017

በአውሮፓ ህብረትና ቱርክ መካከል ወደ አውሮፓ የሚፈልሱ ስደተኞችን አስመልክቶ የተደረገ ስምምነት አንድ ዓመት በኃላ ህጻናት ስደተኞች ተገደው እንዲመለሱ ፣ እንዲታሰሩና እንዲሰቃዩ የሚያስገድድ አስከፊ ሁኔታ እንደገጠማቸው የዓለም የህጻናትና ጉዳይ ድርጅት (ዩኒሴፍ) አስታወቀ፡፡

“ከመጋቢት 2016 በኃላ ወደ አውሮፓ የሚገቡ ህጻናት ስደተኞች ቁጥር ቢቀንስም ፣ የሚያጋጥማቸው ስጋትና ችግር ግን ጨምረዋል” ይላሉ የአካባቢው የዩኒሴፍ ተጠሪ አፍሻን ከሃን፡፡

የግሪክ መንግስትና በሰብአዊ መብት ጉዳይ የሚሰሩ ሸሪኮቹ ብዙ ጥረት ቢያደርጉም በግሪክ ከሚገኙ 2100 ህጻናት ስደተኞች ግማሾቹ በአስቸጋሪ ሁኔታ ተይዘው እስር ቤቶች ውስጥ ይገኛሉ፡፡

“ስደተኞች በመሆናቸው ለእስር የሚዳረጉ ህጻናት እየበዙ መምጣታቸው በጣም ያሳስበናል፡፡ በብዙ አገራት ህጻናት ለረጅም ጊዜ ተቀባይነት በሌለው አያያዝ ለእስር ሲዳረጉ አይተናል፡” ይላሉ የዩኒሴፍ የአስቸኳይ ጊዜ አደጋ አስተባባሪ ሉችዮ ሜላንድሪ፡፡

በግሪክ የሚገኙ የዩኒሴፍ ሰራተኞች በመጠልያ ካምፕ ውስጥ የሚገኙ ህጻናት ስደተኞች በአስከፊ ጭንቀትና ድብርት እንዲሁም ግጭትና አመጽ ሆነው እንደተመለከቱ ገልጸዋል፡፡

አብዛኛዎቹ  ግሪክ ውስጥ ተጥለው የሚገኙ ህጻናት ለዓመታት ትምህርታቸው ያቋረጡ ናቸው፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ ዩኒሴፍ ለግሪክ የትምህርት ሚኒስቴር ድጋፍ በመስጠት በሃገሪቱ ትምህርት ቤቶች እንዲማሩ እየጣረ ነው፡፡