አፍሪካውያን በሊቢያ በሃራጅ መልክ በባርያ ንግድ ይሸጣሉ
TMP – 22/04/2017
ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (IOM) በሊቢያ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ስደተኞች በባርያ ንግድ እስከ 500 ዶላር በገበያ እንደሚሸጡ ገልጿል፡፡
ስደተኞች ገንዘብ ከፍለው እንዲለቀቁ በእስር እንደሚያዙ፤ በተጨማሪም ለጾታ ግንኙነት ጥቃትና የግዳጅ ስራ ይጋለጣሉ ብሏል ድርጅቱ፡፡
ድርጅቱ ዋና የህገወጥ ስደት መዘዋወርያ በሆነችው ሰብሀ ከተማ በገበያ ተሸጠው በጋራዥና የመኪና ማቆሚያ ስፍራ በስራ የተሰማሩ ምዕራብ አፍሪካውያን ስደተኞችን ያነጋገረ ሲሆን ስደተኛች እንደ ዕቃ ገበያ ላይ ከ200 እስከ 500 ዶላር እንደሚሸጡ በሊቢያ የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (IOM) ተልእኮ ኃላፊ ኦትማን በልበሲ ተናግረዋል፡፡
“ሰዎችን በገበያ መሸጥ ሊቢያ ውስጥ በሚገኙ ህገወጥ አዘዋዋሪዎች መካከል እየተለመደ መጥቷል፤ በሃገሪቱ የህገወጥ አዘዋዋሪዎች መረብ እየተጠናከረ በመምጣቱ፡” ብለዋል ኃላፊው፡፡ ህገወጥ ስደተኛች ሴቶችን ስንጠይቅ አስከፊ የሆነ ሰብአዊ አያያዝ ፤ አስገድዶ መድፈርና ፤ ሴተኛ አዳሪነትን የተመለከቱ ንግግሮች ሰምተናል ሲሉም አብራርተዋል፡፡
በባርያ ንግድ የተሸጡ ሴኔጋላውያን ስደተኞች፤ በገበያ ከተሸጡ በኃላ ወደ ሌላ እስር ቤት ተወስደው፤ ያለምንም ክፍያ በቂ ያልሆነ ሬሽን እየተሰጣቸው የጉልበት ስራ እንደሚሰሩና ቤተሰቦቻቸውም ገንዘብ ከፍለው እንዲያስለቅቁዋቸዉ እንደሚገደዱ ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ ከስደተኞቹ ባገኘው ምስክርነት ለአጋቾቻቸው ህገወጥ አዘዋዋሪዎች መክፈል ካልቻሉ ወይ ይገደላሉ ወይም ለሞት ለሚያጋልጥ ችግር ይዳረጋሉም ብሏል፡፡
ሞሃመድ አብዱከር የተባሉ የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (IOM) የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ኃላፊ ለዘጋርድያን ጋዜጣ ሲናገሩ “ሁኔታዉ በጣም አደገኛ ነው፤ ሊቢያ ውስጥ ብዙ በቆየን ቁጥር በዛው ልክ የብዙ ስደተኞች የእንባ ጎርፍ አይተናል፥” ብለዋል፡፡
በህገወጥ አዘዋዋሪዎች እጅ የገቡ ስደተኞች፤ ለግድያ፤ አስገድዶ መደፈርና በቂ ያልሆነ ምግብ ይጋለጣሉም ብለዋል፡፡ ጁሰፔ ሎፕሬኔ የተባሉ በኒጀር የ IOM ሰራተኛ፡ “ብዙ ስደተኞች ከሊቢያ ወደ ሃገራቸው ለመመለስ የሚፈልጉበት ዋና ምክንያት በዚያች ሃገር የሚያጋጥማቸው አስከፊ ችግር ነው ብለዋል፤ ሁኔታዎች እንዲህ ከቀጠሉ በሚቀጥሉት ወራት ብዙ አሳዛኝ ታሪኮች እንደምንሰማ ይጠበቃል፡” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በሊቢያ ያለው አስከፊ ችግር በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ አማራጭ ያጡ ስደተኞች ወደ ጎረቤት ሃገር ቱኒዝያ በጊዚያዊነት ተጠለው በ IOM ድጋፍ ወደ ሃገራቸው ለመመለስ እንደሚሰደዱም ተገልጿል፡፡
በኒጀር የሚገኝ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (IOM) 1500 ስደተኞች በዚህ ዓመት ወደ ሃገራቸው የመለሰ ሲሆን ይህም በ2015 ከመለሳቸው ስደተኞች ቁጥር እንደሚልቅ ተገልጿል፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ