ጣልያን ለሊቢያ ባህር ክልል ጠባቂዎች የምትሰጠዉ የመጀመሪያዉ ዙር ስልጠና አጠናቀቀች

TMP – 24/02/2017

ጣልያን ከሊቢያ እየተነሱ ወደ አዉሮፓ የሚጓዙ ስደተኞች ለመግታት የሚያስችል ለሊቢያ የባህር ክልል ጠባቂዎች የምትሰጠዉ የመጀመሪያዉ ዙር ስልጠና አጠናቀቀች፡፡

78 አባላት ያሉት የሊቢያ ባህር ክልል ጠባቂዎች ቡድን ስልጠናዉን የጀመረዉ በጥቅምት 26፡ 2016 በሳን ጆርጆ እና ሮተርዳም በተባሉ የጣልያንና የሆላንድ መርከቦች ነዉ፡፡ ስልጠናዉ ኦፕሬሽን ሶፊያ በመባል የሚታወቅና የአዉሮፓ ህብረት ከሰሜን አፍሪካ እየተነሱ ወደ አዉሮፓ የሚጓዙትን ስደተኞች ለመግታት ያቀደዉ መርሃ ግብር አካል ነዉ፡፡

ስልጠናዉን አስመልክተዉ በሮም ለፓርላማ ኮሚቴ ንግግር ያደረጉት የጣልያን የሃገር ዉስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሚኒቲ ጣልያን የባህር ክልል ጠባቂዎች ከዛች ሃገር እየተነሱ ወደ ጣልያን የሚገቡትን ስደተኞች ለመግታት የሚያስችል ስልጠና መስጠት ነዉ ብለዋል፡፡ “ሊቢያዉያን ዓቅማቸዉ የሚያጠናክር ስልጠና ከሰጠናቸዉ ለመተባበር ዝግጁ ናቸዉ” ሲሉም ለፓርላማው ኮሚቴ ተናግረዋል፡፡

የስልጠናው ዋና ዓላማ የሊቢያ የባህር ክልል ጠባቂዎችን በማጠናከር ህገወጥ የሰዉ ንግድ አዘዋዋሪዎችን መረብ ለመበጣጠስና ፀጥታን ለማጠናከር ነዉ፡፡ ስልጠናው በሊቢያና በአዉሮፓ ህብረት በፌብሪዋሪ የተደረሰዉ ስምምነት አካል ነዉ፡፡

በጥር 3 የአዉሮፓ መሪዎች ህገወጥ አዘዋዋሪዎችንና ስደተኞችን ለመግታት የሊቢያን ብሄራዊ የባህር ክልል ጠባቂን በስልጠናና በማቴሪያል ለማጠናከር መወሰናቸዉ ይታወቃል፡፡ ዕቅዱ ከግብፅና ቱኒዚያ ጋር ተቀራርቦ በመስራት ሌሎች የህገወጥ ስደት መተላለፍያ መንገዶች ለመዝጋትና በሊቢያ አዲስ የስደትኞች መጠለያ ለማቋቋም የሚሉትንም የሚያካትት ነዉ፡፡
የማልታ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆሴፍ ሙስካት የአዉሮፓ ህብረትና የሊቢያ ስምምነቱን “ህገወጥ ስደትን ለመቆጣጠር የሚያስችል የመጀመሪዉ ኢላማ” ሲሉ፡ የአዉሮፓ ካዉንስል ፕሬዝዳንት ዶናልድ ታስክ ደግሞ “የመጀመሪዉ ትክክለኛና እዉነተኛ ተግባር ነዉ፡”  ብለዋል፡፡