ቢያንስ 126 ስደተኞች ሜዲትራንያን ላይ ሞተው ሊሆን እንደሚችል ተሰግቷል
ቢያንስ 126 የሚሆኑ ስደተኞች ጀልባቸው ከሊቢያ የባህር ጠረፍ ከተነሳች ከሰዓታት በኋላ ሜዲትራንያን ባህር ላይ ሞተው ሊሆን እንደሚችል መሰጋቱ ዓለምአቀፍ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ገለፀ።
ከአደጋው የተረፉት ሁለት ሱዳናውያን እና ሁለት ናይጄርያውያን እንዳሉት የጎማ ጀልባዋ ከሊቢያ ስትነሳ በብዛት ሱዳናውያን የሚገኙባቸው 130 ሰዎች ተሳፍረውባት ነበር።
እነሱ እንደሚሉት፤ በባህር ላይ ለጥቂት ሰዓታት ከተጓዙ በኋላ አንድ የሊቢያዎች ቡድን መጥቶ የጀልባይቱን ሞተር ሰረቀ። ካለ ሞተር ባህሩ ላይ እየተንሳፈፈች ሳለች፤ ማዕበል መጥቶ ከአቅም በላይ የተጫነችውን ጀልባ ስላናወጣት ሰመጠች፡፡
“[ሊቢያውያኖቹን] የባህር ወንበዴዎች ብለው ነው የገለፅዋቸው፤ ነገር ግን በመሰረቱ የሰው አዘዋዋሪዎች ናቸው፡” ብለዋል የ አይኦኤም ቃል አቀባይ ፍላቭዮ ዲ ጃኮሞ።
አራቱ ከአደጋው የተረፉትን ሰዎች የኢጣልያ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች ያዳኗቸው ሲሆን በመጨረሻም ወደ ሲሲሊ ተወስደዋል፡፡
“ደንግጠው ነበረ፤ በተፈጠረውም ነገር ተጨንቀውና እጅጉን ተዳክመው ነበር፡” ብለዋል ዲ ጃኮሞ።
“ጀልባዋን ካለሞተር ባህሩ ላይ ጥሎ መሄድ ግድያ ከመፈፀም ጋር እኩል ነው፡” በማለት ይቀጥላሉ።
“ሞተሩ የተሰረቀው መጀመርያውኑም ታንኳይቱን መንገድ ባስጀመሩ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች በራሳቸው አልያም ደግሞ በተቀናቃኝ ቡድን ነው ብለን እናምናለን። ባለፉት ስድስት ወራት ሞተራቸው የሚሰረቁ ጀልባዎች ቁጥር ከፍ ማለቱን ታዝበናል። ለአዘዋዋሪዎቹ ትልቅ ዋጋ ያላቸው ነገሮች ናቸው፡” ሲሉ አክለዋል፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ