የመንግስታቱ የስደተኞች ድርጅት አፍሪካውያን ስደተኞችን ለመርዳት 421 ሚሊዮን ዶላር ጠየቀ

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) ወደ አውሮፓ የሚጓዙ አፍሪካውያን ስደተኞችን ለመጠበቅና ትርጉም ያላቸው አማራጮችን ለመፍጠር ያስችለው ዘንድ የ 421 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ጠይቋል።

UNHCR ከሰሃራ-በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገሮች የሚገኙ ስደተኞችን እንዲሁም የሰሃራ በረሃንና የሜዲትራንያን ባህር የሚያቋርጡ ስደተኞችን አጠባበቅ ለማሻሻል እንደሚፈልግ ተናግሯል።

“በሰሃራ እና በሜዲትራንያን የሚደረገው የስደተኞች ጉዞ እጅግ ዘግናኝ በሆነ መልኩ የሰው ሂወት እያስከፈለ ነው የሚገኘው” ብለዋል የዩኤንኤችሲአር የመካከለኛው ሜዲትራንያን ጉዳዮች ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ቪንሰንት ኮቼቴል።

“ለዚህ ጉዞ ትርጉም ያላቸው እና ተግባራዊ ሊደረጉ የሚችሉ አማራጮችን ማቅረብ ይጠበቅብናል ካልሆነ ግን ሞት እና ስቃዩ መጨመሩን ይቀጥላል። ወደ ሊቢያ በሚያመሩ ብዙ የጉዞ መስመሮች ላይ የሚገኙ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን መጠበቅ የሚያስችሉ ውጤታማ መንገዶችና ዘዴዎችን ለማቅረብ የሚያስችሉ ነባር እና አዳዲስ እንቅስቃሴዎች ማዳበር እንፈልጋለን፤ እንዲሁም ደግሞ በነዚህ ሁሉ ጥረቶች ውስጥ ባለድርሻ አካላት የሚያደርጉትን ተሳትፎ መደገፍም እንፈልጋለን” ሲሉ ኮቼቴል ጨምረዋል።

የገንዘብ ድጋፉ ህገወጥ ስደት ስለሚያስከትላቸው አደጋዎች ግንዛቤ ለመፍጠር፣ መሰል ጉዞ ለማድረግ ይበልጥ ተጋላጭ ከሆኑ የማህበረሰብ አባላት ጋር የሚደረግ የመረጃ ልውውጥ ለማሻሻል፣ የህግ አፈፃፀም መንገዶችን ለመደገፍ፣ ህገወጥ የሰው ዝውውርን ለመቆጣጠር እንዲሁም ከባህር ላይ ለሚታደጉ ስደተኞች ሰብኣዊ ዕርዳታ መደረጉን ለማረጋገጥ የሚውል ነው።

ዩኤንኤችሲአር፤ በሰሜናዊ አፍሪካ የስደተኞችን አጠባበቅ ማሻሻል፣ ለሊቢያ የባህር ጠረፍ ጥበቃ አገልግሎት የሰልጠና ድጋፍ ማድረግ እና ከባህር ላይ ለሚታደጉ ስደተኞች ሰብኣዊ ዕርዳታ መደረጉን ማረጋገጥ ይፈልጋል።

በሊቢያ በኩል አቋርጠው ወደ አውሮፓ የሚደርሱ አፍሪካውያን ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ፤ እነዚህ ስደተኞች ላይ የሚያጋጥሙ አደጋዎችም በዚሁ ልክ ጨምረዋል። ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ፤ ቢያንስ 2,170 የሚሆኑ ስደተኞች በመካከለኛው ሜዲትራንያን ሞተዋል አሊያም ደግሞ ጠፍተዋል፤ ሌሎች ብዙዎች ደግሞ የሜዲትራንያን የባህር ጠረፍ ላይ እንኳን ሳይደርሱ እንደሞቱ ይታመናል።