50 የሚደርሱ ስደተኞች በየመን ጠረፍ ሆን ተብሎ ወደ ባህር እንዲሰምጡ ተደረገ
ከሶማሊያና ኢትዮጵያ የመጡ ቢያንስ 50 የሚሆኑ ስደተኞች በየመን ጠረፍ በህገወጥ የሰው አዘዋዋሪው በግድ ወደ ባህሩ ከተገፈተሩ በኋላ ሆን ተብሎ እንዲሰምጡ ተደርገዋል፡፡ ዓለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት (IOM) ድርጊቱን “አስደንጋጭ እና ኢሰብኣዊ” ብሎታል፡፡
የ IOM መግለጫ እንዳመለከተው፤ የድርጅቱ ሰራተኞች መደበኛውን ቁጥጥር በሚያደርጉበት ጊዜ የ 29 ሟች ስደተኞችን መቃብር አግኝቷል፡፡ ሟቾቹ የተቀበሩት ከአደጋው በተረፉት ሰዎች ነው፡፡ አይኦኤም፤ ቢያንስ 22 የሚሆኑ ስደተኞች እስካሁን የገቡበት አልታወቀም ያለ ሲሆን፤ የድርጅቱ ሰራተኞች ከአደጋው ተርፈው በባህር ዳርቻው ላይ ለቆዩት ሰዎች ድጋፍ ሰጥተዋል ሲል አክሏል፡፡
ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪው፤ ወደ የመን የባህር ጠረፍ አቅራቢያ ሲደርሱ ስደተኞቹን ወደ ባህሩ እንዲዘሉ አስገደዳቸው ይላል የ IOM መግለጫ፡፡
“ከአደጋው የተረፉት ሰዎች ባልደረቦቻችንን በባህር ዳርቻው ላይ እንደነገርዋቸው፤ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪው በጠረፉ አካባቢ ‘ተቆጣጣሪ የሚመስሉ’ አንዳንድ ሰዎችን ሲያይ ወደ ባህሩ ገፈተራቸው” ብለዋል በየመን የአይኦኤም ልዑክ ኃላፊ የሆኑት ላውረንት ዴ ቦይክ፡፡
“በተጨማሪም ህገወጡ የሰው አዘዋዋሪ ስራውን ለመቀጠል እና ተጨማሪ ስደተኞችን በዚሁ መንገድ ወደ የመን ለማጓጓዝ ወደ ሶማሊያ መመለሱን ነግረውናል” ብለዋል፡፡
ፅሑፉን ያካፍሉ