የ 33,000 ሟች ስደተኞች ዝርዝር በጀርመን ጋዜጣ ታተመ

ሜዲትራንያንን ለማቋረጥ ሲሞክሩ የተያዙ ስደተኞች፡፡ ፎቶ፡ Getty Images

አንድ የጀርመን ጋዜጣ ወደ አውሮፓ ለመድረስ ሲሞክሩ የሞቱ የ 33,293 ሰዎችን ዝርዝር አትሟል፤ ይህም አደገኛውን ጉዞ ለማመላከት ነው፡፡

ይህ ዝርዝር የተዘጋጀው ባኑ ሴኔቶጉሉ በሚባል ታዋቂ የቱርክ አርቲስት ሲሆን፤ ዝርዝሩም ከ 1993 እስከ ሰኔ 2017 ባለው ጊዜ ወደ አውሮፓ ሲጓዙ ሂወታቸውን ያጡ የእያዳንዱን ስደተኞች ስም፣ ዕድሜ፣ ፆታ፣ ዜግነት እና የሞት መንስዔ ያካተተ ነው፡፡
ይህ ዝርዝር መዘጋጀቱ፤ ጉዳዩ ከአሃዛዊ መረጃ ባሻገር የዚህን የስደተኞች ቀውስ ሰብኣዊ ገፅታ ለዓለም ለማሳየት ይረዳል የሚል ተስፋ እንዳለው ዴር ታገስፒገል ጋዜጣ ተናግሯል፡፡

ይህ ዝርዝር ሲዘጋጅ ከ 500 በላይ ቡድኖች እና ግለሰቦች መረጃ በማሰባሰብ ስራ ላይ ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን፤ ዝርዝሩ አሁንም ቢሆን “ከባህር በማንኪያ” ብቻ ነው ሲል ሴኔቶጉሉ ለጋዜጣው ተናግሯል፡፡

ያለፈው ዓመት ሜዲትራንያንን ለሚያቋርጡ ስደተኞች ከስካሁኑ እጅጉን አደገኛ ዓመት ነበር፡፡ ዓለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት (IOM) ባወጣው ዘገባ መሰረት፤ ከ 5,000 በላይ ስደተኞች ወደ አውሮፓ በመጓዝ ላይ እንዳሉ ሞተዋል፤ አሊያም ደግሞ የገቡበት አልታወቀም፡፡

የአፍጋኒስታን የስደተኞች ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት አላሚ ባልኪ በሰጡትና አርያና ቴሌቪዥን ላይ በታተመው መግለጫ መሰረት፤ ከአጠቃላይ የህገወጥ ስደተኞች ቁጥር 12% የሚሆኑት የአፍጋኒስታን ዜግነት ያላቸው ሲሆኑ፤ አብዛኞቹ ደግሞ ወደ አውሮፓ ለመድረስ የሚሞክሩ ናቸው፡፡