የኤርትራ ድያስፖራ አባላት በሊብያ በኤርትራውያን ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ አወገዙ

ሊብያ ላይ ባሉ ብዛት ያላቸው የታገቱ ኤርትራውያን ስደተኞች ምክንያት 200 የኤርትራ ዲያስፖራ ተወካዮች ለአውሮፓ ህብረት ስሞታ አቅርበዋል። ስሞታው የታገቱትን ኤርትራውያን ይለቀቁ ዘንድ የሚጠይቅ ነው።  

እነዚህ የዲያስፖራ አባላት በአመቱ መጨረሻ ከደሰምበር ወር 12-14 ቀን ባለው ጊዜ ውስጥ በቤልጄምዋ መዲና ብራስለስ ከተማ በተካሄደው ኮንፈረንስ ነው ይሄንን ሰሞታ ያቀረቡት። ኮንፍረንሱ “ እኛ ህዝቦች፡ ሰላም ለአፍሪካ ቀንድ! ድህንነት ለኤርትራውያን” በሚል መሪ ቃል ነበር የተካሄደው።  በኮንፈረንሱ ሊብያ በሚገኙ ኤርትራውያን ላይ እየደረሰ ያለ ከፍተኛ የመብት ጥሰት፣ እንግልት እና ህጋዊ ያልሆነ የማጎር ተግባራት አውግዘዋል። ይሄንን ከፍተኛ ስቃይ ለመከላከል የምያስችሉ ምክረሀሳቦችም ሰጥተዋል። ከተሰጡት ምክረ ሃሳቦች ከአውሮፓ ህብረትጋር ያለ ግኑኝነት ማጠናከር እና ኤርትራ ውስጥ ስራ በመስራት ወጣቶች ወደ ስደት እግራቸው የማያነሱበት ዕድል መፍጠር የሚሉ ይገኙባቸዋል።   

አብርሃለይ ተስፋይ የተባለ  ከኤርትራ ተነስቶ በሊብያ በኩል ጣልያን ሃገር የደረሰ እና እዛ የሚኖር ኤርትራዊ ሁኔታው በእንዲህ መልኩ ይገልፀዋል። “የሊብያ ትውስታዬ በጣም መጥፎ ነው።   ኤርትራውያን ይሰቃያሉ። ይራባሉ። ይጠማሉ። የህክምና አገልግሎት ይነፈጋሉ። ቶርቸር ይደረጋሉ። በሺዎች በሚቆጠር ዩሮ ይሸጣሉ ወዘተ።” ብለዋል፤ ለአፈጣኝ ድጋፍ ጥሪውን ስያስተላልፍ። “በአፈጣኝ ከዚህ መውጣት አለባቸው”ም ብለዋል።    

ሌላው ታዋቂው የሰብአዊ መብት ተሟጓች ሙሴ ዘርአይ በኮንፈረንሱ ላይ ተገኝቶ በተለይም ለአውሮፓ ህብረት ባስተላለፈው መልእክት    እንደገለፀው “አውሮፓ በሊብያ እስርቤቶች ለሚማቅቁ ስደተኞች አይንዋ መጨፈን የለባትም። እነዚህ ከ10 ሺ በላይ የሚሆኑ ኤርትራውያን ስደተኞች ካሉበት ማቅ ውስጥ ሊያስወጣ የሚችል የሆነ ስልት መዘየድ ያስፈልጋል።  አብዛኛዎቹም ህፃናት የያዙ ስለሆኑ ወደተሻለ ቦታ ማውጣት የግድ ይላል” ብለዋል።

ከኮንፈረንሱ በኋላ የወጣው መግለጫ “አሁን ኤርትራ እና ኢትዮጵያ የፈጠሩት አዲስ የሰላም ሁኔታ ህገ ወጥ ስደትን ሊያግት አልቻለም፤ እንደጨመረ ነው። አሁንም ቢሆን ብዙ ኤርትራውያን የኢትዮጵያ ድንብር እየተሻገሩ አውሮፓ የምያደርሳቸው የሊብያ መንገድ ለማግኘት እየጎረፉ ናቸው። እንደ ኤመርጀንሲ ሪስፖንስ ኮኦርድኔሽን ሴንተር ዘገባ ከሆነ የኢትዮ ኤርትራ ድንብር ከተከፈተበት ከወርሀ መስከረም ወዲህ 24 ሺ ስደተኞች በኢትዮጵያ በኩል ከኤትራ ወጥተዋል።

   በኮንፈረንሱ የተገኙ የአፍሪካ መሪዎች በኤርትራ እና በሊብያ ያለ ሁኔታ ምን ያህል እንደምያሳስባቸው ገልፀዋል። የፓንአፍሪካን ፓርልያመንት ምክትል ፕረዚደንት የሆኑትን ችግ ፎርቹዩን ቻሩምቢራ  እንዳሉት “የብዙ ስደተኞችን ታሪክ ስሰማ ነበር። በእውነቱ ለመስማት የሚሰቀጥጥ ታሪክ አላቸው። የአይን እማኞችም ስደተኞቹ ያሉበት ሁኔታ ዘመናዊ የባርያ ስርዓት በአፍሪካ ምን እንደሚመስል ማሳያ መሆኑን ይገልፃሉ።”  ሲሉ ተደምጠዋል። አክለውም “ባለን አቅም ሁሉ ዘመናዊ የባርያን ስርዓት ከአፍሪካ ለማስወገድ መስራት አለብን” ብለዋል።

በ2018 ብቻ በሜዲትራንያን መስመር ከሞቱት 4500 ስደተኞች፤ የኤርትራውያን ቁጥር ከፍተኛ እንደሆነ ተገልፀዋል። እንደ አለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም ገለፃ ከሆነ ስደተኞች በዚህ ጉዞ ላይ ህይወታቸው እንድያጡ ከምያደርጉ ፈተናዎች አንዱ የውሃ ጥም ነው። ርሃብ፣ የተሽከርካሪ አደጋ፣ ፊዚካላዊ ጥቃት፣ በሽታ እና የህክምና እጦት፣ መውደቅ፣ እስር እና ሃይፖትሪማ የሞት ምክንያቶች ናቸው።

TMP – 12/01/2019

ፎቶ: ስደተኞች ወደ አውሮፓ ሲሄዱ