የፈረንሳይና ስፔይን የፀጥታ ሃይሎች አንድ የደላላዎች መረብ በመበጠስ 29 ህገ ወጦችን አስሯል

የፈረንሳይና ሰፔይን የፀጥታ ሃይሎች ከአውሮጳ ህብረት የህግ ማስከበርያ ተቋም ጋር በመተባበር፤ አንድ የህገ ወጥ ደላሎች መረብ በመበጣጠስ 29 አባላቶቹን በቁጥጥር ስር አውሏል።

የህገ ወጥ ደላሎች መረብ ሊገኝ የቻለው፤ አንድ የስፔይን ተወላጅ በፈረንሳይ ውስጥ 22 ስደተኞችን በአውቶቡስ አሳፍሮ ሲንቀሳቀስ ከተያዘ በኋላ ነው። በጉዳዩ ላይ ተመስርቶ በስፔይን የተደረገ ምርመራ እንዳጋለጠው፤ ከሞሮኮ እስከ ስፔይንና ፈረንሳይ የተዘረጋ ህገ ወጥ የደላሎች መረብ ተገኝቷል።

ይህ የወንጀለኞች መረብ፤ የተለያዩ አገራት ዜጎች በቅጥረኝነትና በደላላነት በመመልመል፤ ህገ ወጥ ስድተኞችን ወደ አውሮጳ አገራት በአደገኛው የሞት መስመር ለማጓጓዝ ሲያሳምን የቆየ ህቡእ ቡዱን ነበር። በዚህም መሰረት ስድተኞቹ ከስፔይን አልሜርያ ወደብ ወደ ፈረንሳይ ያጓጉዙዋቸው ነበር።

የአውሮጳ ህብረት ፖሊስ (ኢሮፖል) እንደገለፀው፤  “ ይህ የተደረጀ የወንጀለኞች ቡዱን በስፔይን የእንክብካቤ ማእከላት የነበሩ ለአቅመ አዳም ያልደረሱና መጉዚት የሌላቸው ህፃናት እንደ ዋና ታርጌት ተጠቅሟል። ይህ የማፍያ ቡድን በእንክብካቤ ማእከላት የሚገኙ ህፃናቶችን በማባበል ከማእከሉ እንዲያመልጡና ወደ አደገኛው የስደት ጉዞ እንዲቀላቀሉ ያደርጓቸው ነበር “  ሲል ኢሮፖል ጨምሮ ገልፀዋል።

በዚህ ቅፅበታዊ ኦፕረሽን፤ “ በስፔይን ውስጥ 26 ፤ በፈረንሳይ ደግሞ 3 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፤ በተደረገው የ14 የቤት ብርበራ 36,534 የአሜሪከ ዶላር እንዲሁም ወንጀለኞቹ ይጠሙባቸው የነበሩት የተለያዩ ኮምፒተሮች፤ ዶክመንቶች፣መኪና እና 200 ኪሎ ግራም ሓሺሽ ተይዟል።”

ኢሮፖል በቅርቡ አዲስ ፀረ ህገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎችና የተደረጁ ወንጀለኞች ግብረ ሃይል ማቋቋሙን ገልፀዋል። ይህ አዲስ ግብረ ሃይል በአውሮጳ የህገ ወጥ ስድተኞች ዝውውር ማእከል (EMSC) አመካኝነት የተደረጀ ሲሆን ፤ ዋነኛ ታርጌቱ አድርጎ የሚንቀሳቀሰው፤ አደገኛው የህገ ወጥ የሰዎች ድለላ መረብ መበጣጠስ ላይ ነው።

 እነኚህ የህገ ወጥ ዝውውር መረቦች፤ በ2019 ብቻ 46,000 ህገ ወጥ ስድተኞች በአደገኛው የባህር መስመር ወደ አውሮጳ እንዲጓዙ ያመቻቹ ናቸው። ምንም እንኳን በሜዲትራንያን ባህር መስመር ላይ በርካታ ስደተኞች ህይወታቸውን ቢያጡም፤ መስመሩ አሁንም  ደላለዎቹ የሚመርጡት ዋና መስመር በመሆን ቀጥሏል። እንደ አለም አቀፍ የስደተኞች ኮምሽን ሪፖርት ከሆነ፤ በሜዲትራንያን ባህር በዚህ አመት ብቻ የ900 ህገ ወጥ ስደተኞች ህይወት ጠፍቷል።

TMP 02/10/2019

ፎቶ ክሬዲት፤- ቩልካኖ / ሽተር ስቶክ.ኮም

ጥር 13 2019 በፓልማዴ ማሎርካ ከተማ የፖሊስ መኪና